መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 24፤2016 – ከባለቤቱ ጋር ባለመስማማቱ ከቀድሞ ትዳሯ የወለደቻቸዉን ሁለት ልጆቿን በአውሬ ያስበላው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

???? በአስክሬን የፍረንሲክ ምርመራ መሰረት 99.9 በመቶ ከእናታቸው ጋር ተመሳስሏል

በገብረጉራቻ ከተማ 01 ቀበሌ ታደሰ ሞላ የተባለው የ50 ዓመት ግለሰብ ከባለቤቱ ጋር ባለመስማማት ሁለት ልጆቿን በአውሬ ያስበላው አባት በእስራት መቀጣቱን የሰሜን ሸዋ ዞን ዓቃቢ ህግ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ተከሳሹ ከባሌ ዞን ፊናና ወረዳ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረጉራቻ ከተማ በመምጣት ከቀድሞ ባለቤቷ የ7 እና የ3 ዓመት ልጅ  እድሜ ካላቸዉ ልጆች ጋር አብሮ ለመኖር መስማማቱን ዓቃቢ ህግ አቶ ወልታኔት አሰፋ  በተለይም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።። አቶ ታደሰ ሞላ  ወደ ባሌ ሲናና ወረዳ እንሂድ እና የበርበሬ እርሻ ስላለኝ የተሻለ ኑሮ መኖር እንደሚችሉ ይነግራታል ።

ይሁን እና ግን ውሳኔ ለመወሰን ረጅም ጊዜ የወሰደባት እናት  በመጨረሻም ለመሄድ ትስማማለች። ነገር ግን  አቶ ታደሰ ልጆቹን ይዘን መሄድ አንችልም ለእናትሽ ወይም ለማደጎ ስጫቸው  ቢላትም እናት ልጆቼ ካልሄዱ አልሄድም የሚል ምላሽ በመስጠቷ አለመግባባት መፈጠሩን ዓቃቢ ህጉ ገልጸዋል ።

በዚህም ቂም የያዘው ግለሰብ ባለቤቱ ቁርስ እንዲበላ እና ጎረቤት ለቅሶ እንዲሄዱ ብትጠይቀውም አሞኛል በማለት  ሰበብ በመፍጠር ቤት ውስጥ ይቀራል። በዛም የልጆቹ እናት እና አያታቸው እቤት ዉስጥ አለመኖራቸውን እና ወደ ለቅሶ መሄዳቸውን ካረጋገጠ በኋላ  ሁለቱን ልጆች ገደሎ ሩቅ ቦታ በመጣል በአውሬ እንዲበሉ አድርጎል።

ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ   ወደ ባሌ ዞን ተሸሽግ ቢቆይም ፖሊስ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር  ስር ሊውል መቻሉ ተጠቁሟል።  ህጻናቱ ከተጣሉበት ቦታ  ልብሳቸው  እንዲሁንም  ቀሪ የሰውነት አካል  ላይ የፎረንሲክ ምርመራ አድርጎል ። የምርመራ ውጤትም ላይ 99.9 በመቶ  ከእናታቸው ጋር በመመሳሰሉ እና  ተከሳሹ ድርጊቱን መፈጸሙ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።

በዚህም ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም  የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ ታደሰ ሞላ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ዓቃቢህግ ጽ/ቤት ዓቃቢህግ  አቶ ወልታኔት  አሰፋ  ጨምረውም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *