መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – ደቡብ አፍሪካዊዉ አትሌት ፒስቶሪየስ በነገዉ እለት በምህረት ከእስር ሲለቀቅ ከአልኮል መጠጥ መጠጣት ይታገዳል ተባለ

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ የፓራሊምፒክ ሻምፒዮን ኦስካር ፒስቶሪየስ ፍቅረኛውን ሬቫ ስቴንካምፕን በመግደል ክስ ተመስርቶበት ለዓመታት በእስር ማሳለፉ ይታወሳል፡፡አርብ በምህረት ሲለቀቅ አልኮል ከመጠጣት ወይም ለሚዲያ ቃለ መጠይቅ እንዳይሰጥ ይከለከላል ሲል ማረሚያ ቤቱ አስታዉቋል፡፡

ፒስቶሪየስ እ.ኤ.አ. በ2013 በቫላንታይን ወይም በፍቅረኛሞች ቀን በዋና ከተማው ፕሪቶሪያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመታጠቢያ ቤት በር ላይ አራት ጊዜ በመተኮስ ፍቅረኛዉን ስቴንካምፕን መግደሉ ይታወሳል፡፡አሁን ላይ 37 አመቱ ላይ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2017 የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በስቲንካምፕ ግድያ 13 አመት ከአምስት ወር እስራት ተፈርዶበታል ፣ይህም ከዚህ ቀደም የተጣለበትን ተጨማሪ የስድስት አመት ቅጣት ነበር፡፡

ፒስቶሪየስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ።ፒስቶሪየስ በቤቱ ውስጥ ሰርጎ የገባ ወንበዴ እንዳለ በማሰብ እንዲሁም ፍቅረኛው ስቴንካምፕ አልጋ ላይ ተኝታለች ብሎ መተኮሱን በፍርድ ችሎት ላይ ተናግሯል፡፡በደቡብ አፍሪካ ህግ መሰረት፣ ሁሉም ወንጀለኛ የጠቅላላ ቅጣቱን ግማሽ ያህል ከጨረሱ በኋላ ይቅርታ የማግኘት እድል ይኖረዋል፡፡የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር “አጠቃላይ የይቅርታ ሁኔታዎች” በፒስቶሪየስ ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ ብሏል ፣ በሕዝብ ዘንድ ዘንድ ግን ይህዉ መገለጫ ከፋፋይ ሆኗል፡፡

በይቅርታዉ ወቅት በቀኑ ውስጥ በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ ወደ ቤት እንደሚሄድ ይጠበቃል። አልኮሆል ወይም ሌሎች የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን አይወስድም፡፡በይቅርታ ቦርዱ በተለዩ ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ ግዴታዉ ነዉ፡፡ዲፓርትመንቱ አክሎም “እንደ ሌሎች የተፈቱ ሰዎች፣ ፒስቶሪየስ የሚዲያ ቃለመጠይቆችን ከማድረግ ይከለከላል፡፡

ፒስቶሪየስ ገና የአንድ አመት እድሜ እንኳን ሳይሞላው በጤና እክል እግሮቹ ተቆርጠዋል። በመቀጠል በሰው ሰራሽ ህክምና ላይ ተመርኩዞ በአለም ታዋቂ አትሌት ለመሆን በቅቷል። በፓራሊምፒክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል። በለንደን 2012 ኦሎምፒክ ላይ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ አትሌቶች ጋር ተወዳድሯል። የሬቫ ስቴንካምፕ ግድያ እና ተከታዩ የወንጀል ሂደት በዓለም ዙሪያ ዋና ዜናዎች ተቆጣጥሯል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *