መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – ደቡብ አፍሪካዊዉ አትሌት ፒስቶሪየስ በነገዉ እለት በምህረት ከእስር ሲለቀቅ ከአልኮል መጠጥ መጠጣት ይታገዳል ተባለ

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ የፓራሊምፒክ ሻምፒዮን ኦስካር ፒስቶሪየስ ፍቅረኛውን ሬቫ ስቴንካምፕን በመግደል ክስ ተመስርቶበት ለዓመታት በእስር ማሳለፉ ይታወሳል፡፡አርብ በምህረት ሲለቀቅ አልኮል ከመጠጣት ወይም ለሚዲያ ቃለ መጠይቅ እንዳይሰጥ ይከለከላል ሲል ማረሚያ ቤቱ አስታዉቋል፡፡

ፒስቶሪየስ እ.ኤ.አ. በ2013 በቫላንታይን ወይም በፍቅረኛሞች ቀን በዋና ከተማው ፕሪቶሪያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመታጠቢያ ቤት በር ላይ አራት ጊዜ በመተኮስ ፍቅረኛዉን ስቴንካምፕን መግደሉ ይታወሳል፡፡አሁን ላይ 37 አመቱ ላይ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2017 የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በስቲንካምፕ ግድያ 13 አመት ከአምስት ወር እስራት ተፈርዶበታል ፣ይህም ከዚህ ቀደም የተጣለበትን ተጨማሪ የስድስት አመት ቅጣት ነበር፡፡

ፒስቶሪየስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ።ፒስቶሪየስ በቤቱ ውስጥ ሰርጎ የገባ ወንበዴ እንዳለ በማሰብ እንዲሁም ፍቅረኛው ስቴንካምፕ አልጋ ላይ ተኝታለች ብሎ መተኮሱን በፍርድ ችሎት ላይ ተናግሯል፡፡በደቡብ አፍሪካ ህግ መሰረት፣ ሁሉም ወንጀለኛ የጠቅላላ ቅጣቱን ግማሽ ያህል ከጨረሱ በኋላ ይቅርታ የማግኘት እድል ይኖረዋል፡፡የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር “አጠቃላይ የይቅርታ ሁኔታዎች” በፒስቶሪየስ ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ ብሏል ፣ በሕዝብ ዘንድ ዘንድ ግን ይህዉ መገለጫ ከፋፋይ ሆኗል፡፡

በይቅርታዉ ወቅት በቀኑ ውስጥ በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ ወደ ቤት እንደሚሄድ ይጠበቃል። አልኮሆል ወይም ሌሎች የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን አይወስድም፡፡በይቅርታ ቦርዱ በተለዩ ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ ግዴታዉ ነዉ፡፡ዲፓርትመንቱ አክሎም “እንደ ሌሎች የተፈቱ ሰዎች፣ ፒስቶሪየስ የሚዲያ ቃለመጠይቆችን ከማድረግ ይከለከላል፡፡

ፒስቶሪየስ ገና የአንድ አመት እድሜ እንኳን ሳይሞላው በጤና እክል እግሮቹ ተቆርጠዋል። በመቀጠል በሰው ሰራሽ ህክምና ላይ ተመርኩዞ በአለም ታዋቂ አትሌት ለመሆን በቅቷል። በፓራሊምፒክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል። በለንደን 2012 ኦሎምፒክ ላይ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ አትሌቶች ጋር ተወዳድሯል። የሬቫ ስቴንካምፕ ግድያ እና ተከታዩ የወንጀል ሂደት በዓለም ዙሪያ ዋና ዜናዎች ተቆጣጥሯል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – በአሶሳ ዞን የወለደችውን ልጅ መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመክተት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገች የ12ኛ ክፍል ተማሪ በእስራት ተቀጣች

በቤንሻንጉል ጉሙዝ  በአሶሳ ዞን በአብራሞ ወረዳ የአበንዴ ሚንግዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው  የ23  ዓመት ወጣት እንዲሁም  የ12ኛ ክፍል ተማሪ  ድርጊቱን እንደፈፀመችው የወረዳው ፖሊስ ገልጿል።

ግለሰቧ በዕለተ ዕሁድ ሀምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት  ከሌሊቱ 5:00 ሰዓት  በአብራሞ ወረዳ በአበንዴ ሚንግዳ  ቀበሌ ውስጥ ከጋብቻ በፊት  ልጅ  በመውለዷ ምክንያት ወንጀሉን እንደፈፀመች  የወረዳው ፖሊስ  የመረጃ ስርጭት ባለሙያ ሳጅን ካሳዬ ሀይሌ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል ።

ግለሰቧ ልጁን ከከወለደች  በኃላ በፌስታል በማድረግ በአብራሞ ጸዩ ቀበሌ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መፀዳጃ ቤት በመጣል ህይወት እንዲያልፍ አድርጋለች።

ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ጉዳዩን  ሲመረምር የቆየው የአብራሞ ወረዳ ፖሊስ እና ዓቃቢ ህግ  ለአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ይመሰርታል።

ክሱን ሲከታተል የነበረውም የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሠቧ  ድርጊቱን መፈፀሟን በሠው  እና በሰነድ ማሰረጃ በማረጋገጥ ግለሰቧ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ መወሰኑን ሳጅን ካሳየ ሀይሌ ጨምረው ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኮዬ ፈጬ ላለው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ተጠያቂ አይደለሁም አለ

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮዬ ፈጬ ላይ ለሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እጥረት  የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ቢሮ እንጂ አገልግሎቱ ተጠያቂ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሀንስ ገብሬ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደገለፁት የኤሌክትክ መሰረተ ልማት መደበኛ ግንባታ እንዳይኖር ቤቶቹ ሲሰሩ በከተማው የቤቶች ቢሮ በኩል መሰረተ ልማቱ ባለመሰራቱ አገልግሎቱ ዝርጋታውን ማድረግ አልቻለም ብለዋል።

በአንድ  ብሎክ ላይ አንድ ቆጣሪ የገባው በከተማ  በአስተዳደሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ስጡልኝ ባለው መሰረት በኩል  ከፍለው  የተስተናገዱበት ሂደት ነው ብለዋል ፡፡አንድ ቆጣሪ /ባለ 3 ፌዝ ቆጣሪ/ለአንድ ፎቅ የተሰጠበት ምክንያት የአካባቢው እና የቤቶቹ ግንባታው ሳያልቅ ነዋሪው ቀድሞ ስለገባ ፤የኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ለመገንባት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎች በቤቶች ልማት በኩል ስላልተሟላ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የሚሟላበት ጊዜው በመዘግየቱ ምክንያት መደበኛው የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልፀዋል  ፡፡ይህ የኤሌክትሪክ አገልግሎት  ዝርጋታ  መቼ  ይጠናቀቃል እንዲሁም በሁሉም መኖሪያ ቤት የኤሌክትሪክ ቆጣሪ መቼ ይገባል ብሎ ብስራት ላነሳው ጥያቄ አቶ ዮሀንስ ሲመልሱ የኤሌትሪክ ቅድመ ሁኔታዎች ለመዘርጋት በቤቶች ቢሮ በኩል ሲሟላ እና ሲጠናቀቅ እንደሚሆን ተናግረዋል ፡፡

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተጠናቀቁበት ሁኔታ በዚህ ጊዜ መደበኛውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናል ብለን መናገር አልችልም ነገር  ግን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ አድርገናል ብለዋል፡፡በተጨማሪም የአከፋፈል ስርዓቱ  ሁሉም ነዋሪ እኩል ነው ሚከፍለው በዚህ ጉዳይ ደግሞ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ቢለያይም  የአከፋፈል ሁኔታው ግን  የሁሉም ቤት እኩል መሆኑ ልክ ነው ወይ ሲል ብስራት ጥያቄ ሰንዝሯል።

የአከፋፈል ሁኔታው አገልግሎቱን እንደማይመለከተው እና የአገልግሎቱ ኃላፊነት  የተገጠመው ቆጣሪ  የቆጠረውን ልክ ማስከፈል እና ከተበላሸ ጥገና መስጠት እንደሆነ ጨምረው አቶ ዮሀንስ ገብሬ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል ፡፡

በምህረት ታደሰ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – በጋዛ በእስራኤል ጥቃት የተነሳ የአንድ ቤሰተብ አባል የሆኑ 14 ሰዎች ተገደሉ

እስራኤል በአንድ ሌሊት ሳላ በተባለ ግለሰብ ቤተሰብ ላይ በፈጸመችዉ የቦምብ ጥቃት 14 የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸዉን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ከሌሎች የጋዛ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች በደቡባዊ ጋዛ ከካን ዮኒስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው አል-ማዋሲ አካባቢ በሚገኘው ቤት ውስጥ ተጠልለዉ ይገኛሉ።

የእስራኤል ወረራ በዌስት ባንክ ከትላንትናው ምሽት ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስ ቀጥሏል።በቱልካረም በኑር ሻምስ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ 26 ሰዓታትን ያስቆጠረ ወረራ ተፈጽሟል። የአካባቢው ነዋሪዎች የታገቱትን ሰዎች ብዛት ከፍተኛ ነዉ ሲሉ እየገለጹ ይገኛል፡፡ነገር ግን ትክክለኛውን ቁጥር እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም።

በፍልስጤም ተዋጊዎች እና በወራሪ የእስራኤል ሃይሎች መካከል የታጠቁ ግጭቶች እንደነበር ተዘግቧል።በተጨማሪም፣ በናቡስ፣ በራማላ፣ በኬብሮን እና በቤተልሔም ውስጥ ሌሎች በርካታ የእስራኤል ወታደሮች ወረራን እየፈጸሙ ይገኛል፡፡

የእስራኤል የጋዛ የቦምብ ድብደባ የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 20 ፍልስጤማውያን በካን ዮኒስ እና 4 ራፋህ ተገድለዋል ሲል ዋፋ የሀገር ውስጥ የህክምና ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አንድ ፈንድ ዩኒሴፍ ኃላፊ ካትሪን ራስል በጋዛ የሚገኙ ህፃናትን ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመታደግ ያልዉ ጊዜው እያለቀ ነው ብለዋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 24፤2016 – በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠችው የሶማሌ-አሜሪካዊቷ ከንቲባ ቃለ መሃላ ፈጸመች

በዩናይትድ ስቴትስ ሚኒሶታ ግዛት በሚገኘው የሴንት ሉዊስ ፓርክ ከተማ ምክር ቤት የ27 ዓመቷን ናዲያ መሀመድን ከንቲባ አድርጎ ቃለ መሃላ ፈፅሟል። በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሶማሌ-አሜሪካዊት ከንቲባ ሆና ከሁለት ወራት በፊት መመረጧ ይታወሳል።

ናዲያ መሀመድ ባለፈው ህዳር የተካሄደውን የከንቲባ ምርጫ 58 በመቶ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት አሸንፋለች። በከተማዋ በእድሜ ትንሿ እና የመጀመሪያዋ ጥቁር ከንቲባ መሆን ችላለች። ከማንነቴ በላይ መታወቅ እፈልጋለሁ ስትል ተናግራለች።

ማንነቴ የታሪኬ አንዱ አካል ነው፣ እኔ ባለኝ ነገር ሁሉ እኮራለሁ፣ ነገር ግን ያ ብቸኛው ታሪኬ እንዲሆን አልፈልግም። ያ ሰዎች ንግግራቸውን የሚያቆሙበት እንዲሆን አልፈልግም ስትል ናዲያ መሐመድ ከተመረጠች በኋላ በሚኒያፖሊስ ለሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግራለች። እንደ ከንቲባ ሆና ልታደርጋቸው ካቀዳቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የህዝብ ደህንነት እና ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤቶችን ማቅረብ መሆኑን አንስታለች። ናዲያ ሞሃመድ የ23 ዓመት ወጣት እያለች በ2019 ለከተማው ምክር ቤት ተመርጣለች።

ቤተሰቦቿ በሶማሊያ ያለውን ጦርነት ሸሽተው በ10 ዓመቷ ከኬንያ ካኩማ የስደተኞች ካምፕ የገቡ ሲሆን ከዛም ወደ ሚኒሶታ አቅንተዌ። እ.ኤ.አ. በ2021 ዴቃ ዳልክ በሜይን ግዛት በደቡብ ፖርትላንድ ከተማ የምክር ቤት አባላት የመጀመሪያው ሶማሌ-አሜሪካዊ ከንቲባ ሆኖ መሾሙ ይታወሳል።

ነገር ግን የናዲያ መሐመድ ምርጫ የሚለየው በሕዝብ የተመረጡ የመጀመሪያው ሱማሌ-አሜሪካዊት ከንቲባ ያደርጋታል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 24፤2016 – ከባለቤቱ ጋር ባለመስማማቱ ከቀድሞ ትዳሯ የወለደቻቸዉን ሁለት ልጆቿን በአውሬ ያስበላው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት ተቀጣ

???? በአስክሬን የፍረንሲክ ምርመራ መሰረት 99.9 በመቶ ከእናታቸው ጋር ተመሳስሏል

በገብረጉራቻ ከተማ 01 ቀበሌ ታደሰ ሞላ የተባለው የ50 ዓመት ግለሰብ ከባለቤቱ ጋር ባለመስማማት ሁለት ልጆቿን በአውሬ ያስበላው አባት በእስራት መቀጣቱን የሰሜን ሸዋ ዞን ዓቃቢ ህግ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ተከሳሹ ከባሌ ዞን ፊናና ወረዳ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረጉራቻ ከተማ በመምጣት ከቀድሞ ባለቤቷ የ7 እና የ3 ዓመት ልጅ  እድሜ ካላቸዉ ልጆች ጋር አብሮ ለመኖር መስማማቱን ዓቃቢ ህግ አቶ ወልታኔት አሰፋ  በተለይም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።። አቶ ታደሰ ሞላ  ወደ ባሌ ሲናና ወረዳ እንሂድ እና የበርበሬ እርሻ ስላለኝ የተሻለ ኑሮ መኖር እንደሚችሉ ይነግራታል ።

ይሁን እና ግን ውሳኔ ለመወሰን ረጅም ጊዜ የወሰደባት እናት  በመጨረሻም ለመሄድ ትስማማለች። ነገር ግን  አቶ ታደሰ ልጆቹን ይዘን መሄድ አንችልም ለእናትሽ ወይም ለማደጎ ስጫቸው  ቢላትም እናት ልጆቼ ካልሄዱ አልሄድም የሚል ምላሽ በመስጠቷ አለመግባባት መፈጠሩን ዓቃቢ ህጉ ገልጸዋል ።

በዚህም ቂም የያዘው ግለሰብ ባለቤቱ ቁርስ እንዲበላ እና ጎረቤት ለቅሶ እንዲሄዱ ብትጠይቀውም አሞኛል በማለት  ሰበብ በመፍጠር ቤት ውስጥ ይቀራል። በዛም የልጆቹ እናት እና አያታቸው እቤት ዉስጥ አለመኖራቸውን እና ወደ ለቅሶ መሄዳቸውን ካረጋገጠ በኋላ  ሁለቱን ልጆች ገደሎ ሩቅ ቦታ በመጣል በአውሬ እንዲበሉ አድርጎል።

ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ   ወደ ባሌ ዞን ተሸሽግ ቢቆይም ፖሊስ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር  ስር ሊውል መቻሉ ተጠቁሟል።  ህጻናቱ ከተጣሉበት ቦታ  ልብሳቸው  እንዲሁንም  ቀሪ የሰውነት አካል  ላይ የፎረንሲክ ምርመራ አድርጎል ። የምርመራ ውጤትም ላይ 99.9 በመቶ  ከእናታቸው ጋር በመመሳሰሉ እና  ተከሳሹ ድርጊቱን መፈጸሙ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።

በዚህም ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም  የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ ታደሰ ሞላ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ዓቃቢህግ ጽ/ቤት ዓቃቢህግ  አቶ ወልታኔት  አሰፋ  ጨምረውም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 24፤2016 – በኢትዮጵያ 13 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የደም ማነስ እንዳለባቸው ተነገረ

በኢትዮጵያ 50 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የፎሊክ አሲድ እጥረት ያለባቸው ሲሆን 13 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የደም ማነስ እንዳለባቸው ተነግሯል ።

በተለይም በዚህ ችግር የተጎዱ ነፍሰጡር እናቶች በወሊድ እና ከወሊድ በኋላ ለሚከሰቱ ችግሮች ተጋላጭ ሲሆኑ የሚወለዱ ህፃናትም ለመቀንጨር ወይም ለከፍተኛ የጤና ችግር እየዳረጋቸው ይገኛል ተብሏል ።መንግስት ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር በኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረስ የሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2007 ዓ.ም ይፋ በማድረግ ትግበራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል ።

የሰቆጣ ቃልኪዳን ትግበራ የማስፋፋት ምዕራፍ በመጀመሪያው የ2014 ዓ.ም ብቻ ከ59 ሺህ በላይ ህፃናት ከመቀንጨር መታደግ የተቻለ ሲሆን ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ልጆችን ደግሞ ከሞት መታደግ እንደተቻለ ተገልጿል ።የህጻናት መቀንጨር ችግር አሁንም ከፍተኛ መሆኑንና ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት 39 በመቶ መቀንጨር እንዳጋጠማቸው ከጤና ሚኒስትር ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ያገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

በ40 ወረዳዎች የነበረውን የሰቆጣ ቃልኪዳን የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ 240 ወረዳዎች በማስፋፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ተነስቷል ።የህፃናት መቀንጨር ችግርን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ መከላከል እንደሚቻል ተነግሯል ። ፎሊክ አሲድ ከእርግዝና በፊት እና በኋላ  የሚወሰድ ንጥረ ነገር ነው ።

በአበረ ስሜነህ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 24፤2016 – በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ለጫት የተዘጋጀ የጸረ ተባይ መድኃኒት የጠጡ አምስት ህጻናት ህይወታቸዉ አለፈ

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ አምስት እድሜያቸው ከ2 እስከ 5 የሆኑ ህጻናት ለጫት የተዘጋጀ የጸረተባይ  መድሃኒት ጆሊጁስ መስሏቸው ጠጥተው ህይወታቸው ማለፉ   የኮምቦልቻ ወረዳ ፖሊስ አስታዉቋል፡፡

በትላንትናው ዕለት ከረፋዱ 6 ሰዓት ላይ ሲጫወቱ ቆይተው  ጆሊጁስ  መስሏቸው የተበጠበጠ ለጫት የተዘጋጀ የጸረ ተባይ መድሃኒት ጠጥተው ወዲያውኑ  ህይወታቸው  ማለፉን የኮምቦልቻ ወረዳ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ  ኢንስፔክተር መሃመድ ሙሳ በተለይም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ህይወታቸውን ካጡ ህጻናት መካካል አራት ሴቶች እና አንድ ወንድ ልጅ ሲሆኑ ሁለቱ ህጻናት የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውም ተጠቁሟል።  በዚህ ድርጊት መድሃኒቱን  ቤት ውስጥ አስቀምጣለች የተባለችው  ግለሰብ  በቁጥጥር  ስር ውላ  ምርመራ እየተጣራ  መሆኑም ተነግሯል።

የአምስቱ ህጻናት አስከሬን ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ  ጳውሎስ ሆስፒታል መላኩን  እና የመድሃኒቱን ምንነት  ለማጣራት ወደ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መላኩንም ኢንስፔክተር  መሃመድ ሙሳ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 23፤2016- በቦሌ ክፍለ ከተማ 134 ህጻናትን በመሰብሰብ መጠጥና አደንዛዥ ተግባራትን ሲያለማምዷቸዉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የአዲስአበባ ፖሊስ በሁሉም ክ/ከተሞች ላለፉት 20 ያህል ገደማ ቀናት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ሲፈጽም እንደነበር አስታዉቋል።

ፖሊስ በተመረጡ ሶስት ክ/ከተሞች ማለትም በቦሌ ፣ ቂርቆስ እና የካ ክ/ከተሞች ላይ የከወናቸዉን ህግን የማስከበር ተግባራት ይፋ አድርጓል።

የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ በክ/ከተማቸዉ 134 ህጻናትን በመሰብሰብ መጠጥና አልባሌ ተግባራትን ሲያስደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መናገራቸውን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

ፖሊስ በከወንኩት ህግን የማስከበር ስራም በአዲስአበባ 37 በመቶ የወንጀል ተግባራትን በ 20 ቀናት ዉስጥ መቀነስ ተችሏል ብሏል። እርምጃዉ የቁማር ማጫወቻ ቤቶች ፣ የሺሻ ቤቶች ፣ የንግድ እና የተመረጡ መኖሪያቤቶች ያተኮረ ነበር ተብሏል።

በሌላ በኩል 190 ሲም ካርዶችን በመያዝ ወደ ግለሰቦች ስልክ እየደወሉ የማጭበርበር ስር ሲከዉኑ የነበሩ ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸዉ ተነግሯል። በዘመቻዉ የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች ፣ ሀሰተኛ ገንዘብ ፣ አደንዛዥ እጽ ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች ፣ የሺሻ ማስጨሻዎች ፣ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሽ ጥይቶች ፣ ከ 1ሺህ 700 በላይ የተሰረቁ የሞባይል ስልኮች መያዛቸዉም ተገልጿል።

በበረከት ሞገስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 23፤2016- በኢትዮጲያ ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ህይወታቸውን ያጣሉ ተባለ

በኢትዮጵያ በንፅህና ጉድለት ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ህይወታቸውን እንደሚያጡ የጤና ሚኒስቴር አስታዉቋል፡፡

ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት የኮሌራ በሽታን፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ ታይፎይድና ሌሎች በንጽህና ጉድለት ምክንያት የሚሰራጩ በሽታዎችን ለህጻናት ሞት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ እና ሌሎች ተላላፊ በሽተኛዎች ለመከላከል  ሜዳ ለይ መጸዳዳትና መሽናትን ማስቀረት እና ደህንነቱን የጠበቀ የተሻሻለ መጸዳጃ ቤትን በሁሉም ሰአት በሁሉም ቦታና ሁኔታ መጠቀም በርካታ አይነተኛ ፋይዳዎች አሉትም ተብላል፡፡

ንጽህናን በተገቢው ሁኔታ መጸበቅ የተማሪዎች ከትምህርት ቤት የመቅረት ምጣኔን ይቀንሳል፣ ተማሪዎች በትምህርታቸዉ ዉጤታማ እንዲሆኑ ይረዳል፣የሰዉ ልጅ የመኖር እድሜ ጣርያን ይጨምራል፣ ህጻናትን ሞትን ይቀንሳል፣ ምርትና ምርታማነትን ይጨምራል ሲሉ ሚኒስቴር ድኤታው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የመፀዳጃ ቤት ግንባታዎች፣ አያያዝና አጠቃቀም ትምህርት መርጃ መሳሪያዎቸን በማዘጋጀት የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ሰፊ ስራዎች መሰራም አለበት ተብላል፡፡

በትግስት ላቀዉ