ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ይፋ ባደረገው የጊዜ ማዕቀፍ መሰረትነት፣ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ በዘንድሮው ምርጫ የሚወዳደሩ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳቸው እንደበረቱ ናቸው፡፡
ይህንኑ መነሻ አድርጎ “ የፖለቲካ ማህበራቱ ከፖለቲካው ባልተናነሰ ምን ያህል ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በቂ ትኩረት እየሰጡ ይሆን? ” ሲል ብስራት ሬዲዮ የዘርፉን ባለሞያዎች አስተያየት ጠይቋል፡፡
“ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እውቅና ለመስጠት እቸገራለሁ! ” ያሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋ-ፈራሁ ሽታሁን፣“ የፖለቲካ ማህበራቱ ለህብረተሰቡ በሚበጅ ሀሳብ አልተጠመዱም የሀሳብ ጥራትም የላቸውም ” ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡
የምጣኔ-ሀብት ባለሞያው አቶ ዋሲሁን በላይ በአንፃሩ፣ “ አሁን በኢትዮጵያ ያለው መጠነ-ሰፊ ፖለቲካዊ ቀውስ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከፖለቲካ ባለፈው ለኢትዮጵያ ምጣኔ-ሀብታዊ ችግሮች የሚገባውን ትኩረት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል ” ባይ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ፣’ኢትዮጵያ ብዙ አንገብጋቢ ምጣኔ-ሀብታዊ ችግሮች አሉባት’ የሚሉት ሁለቱ የምጣኔ-ሀብት ባለሞያዎች፣” በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ያሉ የፖለቲካ ማህበራት፣በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት ጠቦ የዋጋ-ንረት እና የኑሮ ውድነት የሚረጋጋበትን፣መሬት ከፖለቲካ ዕቃነት ሊላቀቅ የሚችልበትን ጠንካራ ፖሊሲ አቅርበው በሀሳብ ሙግት ለህዝብ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳብ ይዘው መቅረብ ” አለባቸው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡