???? ባገረሻው ግጭት ከ70 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጋዛ ዳግም ጦርነት በመጀመሩ በጣም ተጸጽቻለሁ ብለዋል።
በማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ ባሰፈሩት መግለጫ መሰረት አሁንም የተኩስ አቁሙ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል። ወደ ጦርነቱ መመለስ እውነተኛ ሰብአዊ የተኩስ አቁም ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ብቻ ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል። ጋዛን የሚያስተዳድረው የሃማስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል የጦር ዘመቻዋን ከጀመረች ወዲህ ወደ 6,000 የሚጠጉ ህጻናትን ጨምሮ ከ14,800 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።
በጥቅምት 7 ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝሮ 1,200 ሰዎችን ሲገድል 240 የሚጠጉ ሰዎችን አግቶ ወደ ግዛቱ መውሰዱ ይታወሳል።ባለፈው ሳምንት ከታጋቾቹ ውስጥ ከ100 በላይ የሚሆኑት የተለቀቁ ሲሆን ፍልስጤማውያን እስረኞችን ከእስራኤላውያን እስር ቤቶች ለማስለቀቅ ተችሏል።በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ለሰባት ቀናት የዘለቀው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ያለተጨማሪ ማራዘሚያ ካበቃ በኋላ በጋዛ ጦርነቱ ቀጥሏል።
በመላው ጋዛ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እና በርካታ ትላልቅ የአየር ድብደባዎች ታይተዋል እንዲሁም ተሰምተዋል። የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው ሮኬቶች በደቡብ እስራኤል ላይ ከጋዛ ሰርጥ ተተኩሰዋል። በጋዛ ታግተው የነበሩትን ሴት እና ህጻናትን ሙሉ በሙሉ ማስለቀቅ ባለመቻሉ ሃማስን የእስራኤል ጦር ተወቃሽ አድርጓል። እርቁ ከማብቃቱ በፊት ሮኬቶች ወደ እስራኤል ተተኩሰዋልም ብሏል።
ሀማስ በበኩሉ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በማፍረስ እስራኤልን በመወንጀል የነዳጅ አቅርቦቶችን ወደ ሰሜን ጋዛ እንዳይደርስ አድርጋለች ብሏል።በጋዛ ሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ ባሉት ሰአታት ውስጥ ቢያንስ 70 ሰዎች በአየር ድብደባ መገደላቸውን አስታውቋል ። በደቡባዊው ከተማ ከካን ዮኒስ በስተምስራቅ የሚገኙ ሰዎች በግብፅ ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ራፋህ እንዲሄዱ የሚያስጠነቅቅ በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት ጋዛን በመቶዎች በሚቆጠሩ ዞኖች የሚከፋፍል አዲስ ካርታ የሰራ ሲሆን ይህም “ለቀጣዩ የጦርነት ደረጃ ዝግጁነት” ሰላማዊ ዜጎችን ለቀው እንዲወጡ የሚፈልጓቸውን አካባቢዎች ለማስጠንቀቅ ይጠቅማል ተብሏል።በኳታር የተኩስ አቁሙን ለማስቀጠል አስቸጋሪ የተባለው ድርድር እንደቀጠለ ምንጮች ተናግረዋል።
ጦርነቱ እንደገና ከመጀመሩ በፊት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለእስራኤል እንደተናገሩት በዚህ ጊዜ ሰላማዊ ዜጎችን በተለየ መንገድ መጠበቅ እስራኤል እንዳለባት ገልፃዋል።በሰሜን ጋዛ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዜጎች ሞት እና የጅምላ መፈናቀል በደቡብም ሊደገም እንደማይገባም አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት ኤጀንሲ እርቁ ካልቀጠለ በቀር ሰብአዊ ጥፋት እንደሚመጣ አስጠንቅቋል። በደቡባዊ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ሁኔታውን አስፈሪ ሱል ገልጿል።
በስምኦን ደረጄ