መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 – ኢኳዶር ቀንደኛ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች

ኢኳዶር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን “እጅግ አደገኛ” የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ከከፍተኛ የጸጥታ እስራት ቤት ማምለጡን ተከትሎ ሁከት በተከሰተባት ሀገር ውስጥ በበርካታ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ አለመረጋጋት ተፈጥሯል።ከህዳር ወር ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦአ በኢኳዶር ጎዳናዎች እና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባ ለ60 ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ዘመቻን በማስጀመር ጆሴ አዶልፎ ማሲያስን ፊቶ እንዲታደን ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በየቀኑ ከሰዓት እላፊ ገደብ ጋር እንደሚተገበር ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ኖቦ በኢንስታግራም ላይ በለቀቁት ቪዲዮ አሸባሪዎች ካሏቸዉ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋዋሪዎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ተግባራቸውን ለመወጣት “ሁሉንም የፖለቲካ እና የህግ ድጋፍ” ለወታደራዊዉ ኃይል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ፊቶ ከ2011 ጀምሮ በተደራጀ ወንጀል፣ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት እና በግድያ ወንጀል የ34 አመት እስራት ተፈርዶበት ነበር።ከማረሚያ ቤት ሲያመልጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2013 ከማረሚያ ቤት አምልጦ ከሶስት ወራት በኋላ እንደገና ተይዟል፡፡በሺዎች የሚቆጠሩ የጸጥታ ሃይሎችን ባሳተፈ ኦፕሬሽን ፊቶ ባለፈው ነሃሴ የፕሬዝዳንት እጩ ፌርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ መገደሉን ተከትሎ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚገኝ እስር ቤት ተዘዋውሯል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -የልደት በዓልና የቤዛ ኩሉ ሥነሥርዓት በሰላም ተጠናቀቀ

በላሊበላ የሚከበረዉ የልደት እና የቤዛ ለኩሉ ሥነሥርዓት በሰላም መጠናቀቁን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል። የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል እና የላሊበላ ልዩ መገለጫ የሆነው የቤዛ ኩሉ ሥነሥርዓት በብፁዓን አባቶች፣ በካህናትና ምዕመናን ታጅቦ መከወኑን ነዉ ጣቢያችን የሰማዉ። በሥነሥርዓቱ ላይ የዉጪ ቱሪስቶች መታደማቸዉንም ለማወቅ ችለናል።

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -ሼህ አብዱ ያሲንን በመግደል የሚጠረጠረው መሀመድ ሽኩር አበባው ይፈለጋል ተባለ

ግለሰቡ እጁን እንዲሰጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል። ተጠርጣረው ያለበትን የሚያውቅ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር አዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል።

አዲስ አበባ ፖሊስ በሼህ አብዱ ሞት የተሠማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው እና ለእምነቱ ተከታዮች መፅናናትን ይመኛል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀሉን ፈፃሚ በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትልና የምርመራ ቡድኖችን አዋቅሮ ክትትሉን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የመኖሪያ አድራሻው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ወረዳ 14 ነዋሪ የሆነው ሟቹ ያሳድጉት የነበረው መሀመድ ሽኩር አበባው ሼህ አብዲ ያሲንን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ይፈለጋል።ስለሆነም መሀመድ ሽኩር አበባው ያለበትን የሚያውቅ ሆነ ማንኛውም መረጃ ያለው በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11 ወይም በነፃ ስልክ ቁጥር 991 መረጃ በመስጠት እንዲተባበር አዲስ አበባ ፖሊስ ያስታውቃል፡፡

በወንጀል የተጠረጠረ ግለሠብን መደበቅ ሆነ እንዲያመልጥ መተባበር የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ያስታውቃል።

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በደህንነት ፍተሻ የተነሳ ከበረራ ታገዱ

የዩናይትድ ስቴትስ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ብዛታቸውን 171 የሆኑ ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች ደኅንነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ከበረራ ተገለው  እንደሚቆዩ አስታውቋል። የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር በአላስካ አየር መንገድ የአውሮፕላን ፍንዳታ አርብ እለት ከደረሰ በኋላ አውሮፕላኖቹ ሲፈተሹ ቆይተዋል።የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የህዝብ ደህንነት መጠበቅ ነው ብሏል።

የቦይንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቭ ካልሁን ለሰራተኞቹ እንደተናገሩት “የኩባንያው ትኩረት መሆን አለበት” ብለዋል። ዋና ዋና የአሜሪካ አየር መንገዶች በደርዘን የሚቆጠሩ አውሮፕላኖችን ከደህንነት ጋር በተያያዘ ከበረራ እንዲቆሙ ማድረጋቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በረራ እንዲሰረዝባቸው ምክንያት ሆኗል።ጉዳት የደረሰባቸውን አውሮፕላኖች አቁመናል፣ ደህና መሆናቸውን እስኪያረጋግጥ ድረስ መሬት ላይ እንዳሉ ይቆያሉ” ሲል የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር በትላንትናው እለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ቦይንግ በበኩሉ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የፊታችን ማክሰኞ የሁሉም ሰራተኞች የደህንነት ስብሰባ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

እንዲህ አይነት ከባድ አደጋዎች ሲከሰቱ የችግሩን መንስኤዎች ለመረዳት እና መፍትሄ ለመስጠት ከደንበኞቻችን እና ተቆጣጣሪዎቻችን ጋር በግልፅ መስራት እና እንደገና እንዳይከሰቱ ለማድረግ ለእኛ ወሳኝ ነው” ሲሉ ካልሁን ተናግረዋል። የአውሮፕላኖቹ ከበረራ መታገድ በዋነኛነት በአሜሪካ በረራዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በአሜሪካ ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በዩናይትድ አየር መንገድ እና በአላስካ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ።

የቱርክ አየር መንገድ፣ የፓናማ ኮፓ አየር መንገድ እና ኤሮሜክሲኮ ተመሳሳይ ሞዴል ያላቸውን አውሮፕላኖች ለምርመራ በሚል አውሮፕላኖቹን ከበረራ አግደዋል። አላስካ አየር መንገድ 65 አውሮፕላኖችን ያገደ ሲሆን በትላንትናው እለት 163 በረራዎችን ወይም 21 በመቶውን የአየር መንገዱን በረራዎች ሰርዟል።ወደ 25 ሺ የሚጠጉ ሰዎች በበረራው መሰረዝ ተጎድተዋል። አየር መንገዱ አንዳንድ አውሮፕላኖቹን ከበረራ መታገዳቸውን ተከትሎ የሚፈጠረው የጉዞ መስተጓጎል ቢያንስ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ድረስ እንደሚቀጥል ተናግሯል።ዩናይትድ አየር መንገድ 79 አውሮፕላኖችን ማገዱን እና እሁድ እለት ወደ 180 የሚጠጉ በረራዎችን መሰረዙን አስታውቋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 30፤2016 -ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎችና ከ2 ቶን በላይ የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ማሽከርከር የማይችሉባቸው መንገዶች ይፋ ሆነዋል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ሞተር ሳይክሎችና ከሁለት ቶን በላይ የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ማሽከርከር የማይችሉባቸው መንገዶችን ይፋ አድርጓል።ክልከላውን በሚጥሱ አሽከርካሪዎች ላይም ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል።

የአዲሰ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ሰሞኑን ለሞተር ሳይክሎችና ከሁለት ቶን በላይ ለሆኑ ተሽክርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶችን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ክልከላው ከቦሌ በኦሎምፒያ መስቀል አደባባይ፣ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት፣ አራት ኪሎ በሁለቱም አቅጣጫ ሲሆን፤ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የትራፊክ ምልክቶች መተከላቸውንም መረጃው ጠቅሷል።

አዲስ የተተከሉት ምልክቶችና ማመልከቻዎች ከ2 ቶን በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች እና ሞተር ሳይክሎችን የሚከለክሉ በመሆኑ፤ በተጠቀሰው መንገድ ከዛሬ ጀምሮ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ አውቀው ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።

የተተከሉ ምልክቶችን ማክበር ከአሽከርካሪዎቹ እንደሚጠበቅ እና ይህንኑ ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል።የተሽከርካሪ ባለንብረቶችም ሆኑ አሽከርካሪዎች ይህን ተገንዝበው ለሕጉ መከበር ግዴታቸውን እንዲወጡ ፖሊስ አሳስቧል።

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2016 – ፍቅረኛውን የገደለው ደቡብ አፍሪካዊው አትሌት ኦስካር ፒስቶሪየስ በይቅርታ ከእስር ተለቀቀ

ፓራሊምፒያን የሆነው ኦስካር ፒስቶሪየስ ፍቅረኛውን ሬቫ ስቴንካምፕን ከገደለ ከ11 ዓመታት ገደማ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝበት ማረሚያ ቤት በይቅርታ በነፃ ተለቋል።

ባለሥልጣናቱ ፒስቶሪየስ ከተፈረደበት ከ13 ዓመታት በላይ የእስር ጊዜውን ውስጥ ግማሹን በማጠናቀቁ ዛሬ ጠዋት መኖሪያ ቤቱ እንደገባ አረጋግጠዋል። የሟቿ ስቴንካምፕ እናት የቀድሞዋን አትሌት ከእስር የመለቀቅ ውሳኔ መቀበሏን ተናግራለች ነገር ግን ቤተሰቦችን በልጃችን ሞት የእድሜ ልክ እስራት ውስጥ ይገኛል ስትል አክላለች። ፒስቶሪየስ እ.ኤ.አ. በ2013 በቫላንታይን ወይም በፍቅረኛሞች ቀን በዋና ከተማው ፕሪቶሪያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመታጠቢያ ቤት በር ላይ አራት ጊዜ በመተኮስ ፍቅረኛዉን ስቴንካምፕን መግደሉ ይታወሳል፡፡

የ29 ዓመቷ ወ/ሮ ስቴንካምፕ የህግ ተመራቂ እና የተሳካላት ሞዴል ነበረች። በቲቪ አቅራቢነት የሰራች ሲሆን ትሮፒካ አይስላንድ ኦፍ ትሬዠር በተሰኘው የቲቪ ፕሮግራም ላይ ስትሳተግ ነበር። በህግ ከተመረቀች በኋላ በደል የተፈፀመባቸውን ሴቶች የሚረዳ የህግ ድርጅት ለመክፈት አቅዳ ነበር።ከፒስቶሪየስ ጋር የነበራት ግንኙነት ለሶስት ወራት ያህል ብቻ ነበር።

አሁን ላይ 37 አመቱ ላይ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2017 የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በስቲንካምፕ ግድያ 13 አመት ከአምስት ወር እስራት ተፈርዶበታል ፣ይህም ከዚህ ቀደም የተጣለበትን ተጨማሪ የስድስት አመት ቅጣት ነበር፡፡ፒስቶሪየስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ።ፒስቶሪየስ በቤቱ ውስጥ ሰርጎ የገባ ወንበዴ እንዳለ በማሰብ እንዲሁም ፍቅረኛው ስቴንካምፕ አልጋ ላይ ተኝታለች ብሎ መተኮሱን በፍርድ ችሎት ላይ ተናግሯል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ህግ መሰረት፣ ሁሉም ወንጀለኛ የጠቅላላ ቅጣቱን ግማሽ ያህል ከጨረሱ በኋላ ይቅርታ የማግኘት እድል ይኖረዋል፡፡ፒስቶሪየስ ገና የአንድ አመት እድሜ እንኳን ሳይሞላው በጤና እክል እግሮቹ ተቆርጠዋል። በመቀጠል በሰው ሰራሽ ህክምና ላይ ተመርኩዞ በአለም ታዋቂ አትሌት ለመሆን በቅቷል። በፓራሊምፒክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል።

በለንደን 2012 ኦሎምፒክ ላይ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ አትሌቶች ጋር ተወዳድሯል። የሬቫ ስቴንካምፕ ግድያ እና ተከታዩ የወንጀል ሂደት በዓለም ዙሪያ ዋና ዜናዎች  ተቆጣጥሯል።

በበረከት ሞገስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2016 – ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ድንበር ደሴት የጦር መሳሪያ መተኮሷ ተሰማ

ሰሜን ኮሪያ ከ200 የሚበልጡ የጦር መሳሪያዎችን በምእራብ የባህር ዳርቻዋ ወደ ደቡብ ኮርያ ደሴት መተኮሷን የሴኡል ጦር አስታወቀ።ደቡብ ኮሪያ ጎረቤቷ ልምምድ ከማድረጓ በፊት ሰላማዊ ዜጎች በደሴቲቱ ላይ መጠለያ እንዲፈልጉ ትዕዛዝ አስተላልፋ ነበር፡፡

ደቡብ ኮርያ ድርጊቱን ጸብ ጫሪ ስትል አዉግዛለች፡፡እ.ኤ.አ. በ2010 የሰሜን ኮሪያ ጦር በዮኦፕዮንግ ደሴት ላይ በርካታ ጊዜ በመተኮሱ አራት ሰዎችን ገድሏል።ዛሬ የተተኮሰው የመድፍ ጥይቶች ወደ ደቡብ ኮሪያ ግዛት አልገቡም ሁሉም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ልዩ ዞን ዉስጥ ወድቀዋል፡፡የደቡብ ኮሪያ የጋራ አዛዦች ክስተቱ “በህዝባችን እና በወታደራዊ ሃይላችን ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም” ቢሉም ድርጊቱ “በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ሰላምን አደጋ ላይ የሚጥል እና ውጥረትን የሚፈጥር ነው” ብለዋል።

ጥቃቱ የፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትጥቅ እየገነባች ነው በማለት በባህረ ሰላጤው ላይ “በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ” ለሚችለው ጦርነት እየተዘጋጀች መሆኑን ማስጠንቀቂያ የሰጠችውን ተከትሎ ነው።በአቅራቢያው ባሉ ሁለት ደሴቶች ላይ ያሉ ባለስልጣናት ሲቪሎች መጠለያ እንዲፈልጉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ሺን ዎንሲክ በዛሬዉ እለት በሰጡት መግለጫ “ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ማለዳ ላይ የመድፍ ልምምዷን ማስቀጠሏ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ሰላምን አደጋ ላይ የሚጥል እና ውጥረትን የሚፈጥር የቅስቀሳ ተግባር ነው” ብለዋል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2016 – በአራዳ ክፍለ ከተማ በተዘጋጀ የገና ባዛር ላይ የአገልግሎት ጊዜያቸው እና ምርታቸው አጠራጣሪ የሆኑ የምግብ ምርቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጀ የገና በጥራታቸው ላይ አጠራጣሪ የሆኑ የምግብ ምርቶች መያዛቸውን እና የናሙና ምርመራ እየተደረገ መሆኑን በአዲስ አበባ የምግብ እና መድሃኒት  ባለስልጣን የምግብ እና ጤና ነክ  ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር   አቶ ሚሬሳ ሚዴቅሳ በተለይም ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለከተማ በሚገኙ የበዓል የገበያ ቦታዎች ላይ ለምግብነት የቀረቡ የባልትና ምርቶች   የአገልግሎት ጊዜያቸው እና በውስጣቸው ስላለው ንጥረ ነገር መግለጫ ጽሁፍ የሌላቸው መሆኑም አጠራጣሪ እንዳደረጋቸው ተጠቁሟል።  

ምርቶቹ ምንም እንኳን የሀገር ውስጥ ቢሆኑም መቼ ፣የት እንደተመረተ ሊገልጽ የሚገባ  ነገር መኖር እንዳለበትም ዳይቴክተሩ  ተናግረዋል። በተጨማሪም  ናሙና ተወስዶ በምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር  ምርምራ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ምርቶች መካከል  ሽሮ፣ በርበሬ እና ማር እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል።

በመሆኑም ለበዓል በተዘጋጁ  የገበያ ቦታዎች ላይ የአገልግሎት ምርት እና ይዘታቸው ያልተለጠፈባቸው ምርቶች  በተመለከተ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቀቄ እንዲያደርግ ተገልጿል ።

ወቅቱ በዓል በመሆኑ  በምግብ ነክ ምርቶች  ላይ  ተገቢውን ቁጥጥር  በልዩ መልክ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን በማንሳት   ህብረተሰብ  አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት ጥቆማ  መስጠት እንዳለበት  አቶ ሚሬሳ ሚዴቅስ ጨምረዉ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – ደቡብ አፍሪካዊዉ አትሌት ፒስቶሪየስ በነገዉ እለት በምህረት ከእስር ሲለቀቅ ከአልኮል መጠጥ መጠጣት ይታገዳል ተባለ

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ የፓራሊምፒክ ሻምፒዮን ኦስካር ፒስቶሪየስ ፍቅረኛውን ሬቫ ስቴንካምፕን በመግደል ክስ ተመስርቶበት ለዓመታት በእስር ማሳለፉ ይታወሳል፡፡አርብ በምህረት ሲለቀቅ አልኮል ከመጠጣት ወይም ለሚዲያ ቃለ መጠይቅ እንዳይሰጥ ይከለከላል ሲል ማረሚያ ቤቱ አስታዉቋል፡፡

ፒስቶሪየስ እ.ኤ.አ. በ2013 በቫላንታይን ወይም በፍቅረኛሞች ቀን በዋና ከተማው ፕሪቶሪያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በመታጠቢያ ቤት በር ላይ አራት ጊዜ በመተኮስ ፍቅረኛዉን ስቴንካምፕን መግደሉ ይታወሳል፡፡አሁን ላይ 37 አመቱ ላይ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2017 የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በስቲንካምፕ ግድያ 13 አመት ከአምስት ወር እስራት ተፈርዶበታል ፣ይህም ከዚህ ቀደም የተጣለበትን ተጨማሪ የስድስት አመት ቅጣት ነበር፡፡

ፒስቶሪየስ ወንጀሉን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ።ፒስቶሪየስ በቤቱ ውስጥ ሰርጎ የገባ ወንበዴ እንዳለ በማሰብ እንዲሁም ፍቅረኛው ስቴንካምፕ አልጋ ላይ ተኝታለች ብሎ መተኮሱን በፍርድ ችሎት ላይ ተናግሯል፡፡በደቡብ አፍሪካ ህግ መሰረት፣ ሁሉም ወንጀለኛ የጠቅላላ ቅጣቱን ግማሽ ያህል ከጨረሱ በኋላ ይቅርታ የማግኘት እድል ይኖረዋል፡፡የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር “አጠቃላይ የይቅርታ ሁኔታዎች” በፒስቶሪየስ ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ ብሏል ፣ በሕዝብ ዘንድ ዘንድ ግን ይህዉ መገለጫ ከፋፋይ ሆኗል፡፡

በይቅርታዉ ወቅት በቀኑ ውስጥ በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ ወደ ቤት እንደሚሄድ ይጠበቃል። አልኮሆል ወይም ሌሎች የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን አይወስድም፡፡በይቅርታ ቦርዱ በተለዩ ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ ግዴታዉ ነዉ፡፡ዲፓርትመንቱ አክሎም “እንደ ሌሎች የተፈቱ ሰዎች፣ ፒስቶሪየስ የሚዲያ ቃለመጠይቆችን ከማድረግ ይከለከላል፡፡

ፒስቶሪየስ ገና የአንድ አመት እድሜ እንኳን ሳይሞላው በጤና እክል እግሮቹ ተቆርጠዋል። በመቀጠል በሰው ሰራሽ ህክምና ላይ ተመርኩዞ በአለም ታዋቂ አትሌት ለመሆን በቅቷል። በፓራሊምፒክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል። በለንደን 2012 ኦሎምፒክ ላይ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ አትሌቶች ጋር ተወዳድሯል። የሬቫ ስቴንካምፕ ግድያ እና ተከታዩ የወንጀል ሂደት በዓለም ዙሪያ ዋና ዜናዎች ተቆጣጥሯል።

በስምኦን ደረጄ

መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 25፤2016 – በአሶሳ ዞን የወለደችውን ልጅ መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመክተት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገች የ12ኛ ክፍል ተማሪ በእስራት ተቀጣች

በቤንሻንጉል ጉሙዝ  በአሶሳ ዞን በአብራሞ ወረዳ የአበንዴ ሚንግዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው  የ23  ዓመት ወጣት እንዲሁም  የ12ኛ ክፍል ተማሪ  ድርጊቱን እንደፈፀመችው የወረዳው ፖሊስ ገልጿል።

ግለሰቧ በዕለተ ዕሁድ ሀምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት  ከሌሊቱ 5:00 ሰዓት  በአብራሞ ወረዳ በአበንዴ ሚንግዳ  ቀበሌ ውስጥ ከጋብቻ በፊት  ልጅ  በመውለዷ ምክንያት ወንጀሉን እንደፈፀመች  የወረዳው ፖሊስ  የመረጃ ስርጭት ባለሙያ ሳጅን ካሳዬ ሀይሌ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል ።

ግለሰቧ ልጁን ከከወለደች  በኃላ በፌስታል በማድረግ በአብራሞ ጸዩ ቀበሌ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መፀዳጃ ቤት በመጣል ህይወት እንዲያልፍ አድርጋለች።

ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ጉዳዩን  ሲመረምር የቆየው የአብራሞ ወረዳ ፖሊስ እና ዓቃቢ ህግ  ለአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ይመሰርታል።

ክሱን ሲከታተል የነበረውም የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሠቧ  ድርጊቱን መፈፀሟን በሠው  እና በሰነድ ማሰረጃ በማረጋገጥ ግለሰቧ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ መወሰኑን ሳጅን ካሳየ ሀይሌ ጨምረው ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ