ጦማር/ዜና

ለኬንያ እጅ ነስተናል

በቻይና የተደረገዉ የዘንድሮዉ የአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻንፒዎና ውድድር ለአፍሪቃ ትልቅ ታሪክ የተሰራበት እና አፍሪቃ በተወሰነ ውድድር አለመወሰኟን ለአለም ያስመሰከረችበት ጊዜ ነበር።

ምንም እንኳን አገራችን በወንዶች ህዝቧ የጠበቀዉን ዉጤት ባታገኘም በሴቶች አስከትላ መግባቷን እና ሬኮርድ መስበሯን የቀጠለችበት ውድድር ነበር። ከሁሉም በላይ ግን ሊወራላት እና እጅ ሊነሳላት የሚገባት ጎረቤቷ ኬንያ ናት።
ኬንያ በዘንድሮ የአለም አቀፍ ውድድር ላይ አፍሪቃ በመላዉ የአትሌቲክስ ውድድርን በተለይ የትራኩን ውድድር ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተወሰኑ ውድድሮች ብቻ እንደቀራት ያሳየችበት ጊዜ ነበር። አፍሪቃ በርቀት ውድድር መረብ ውስጥ እራሷን ወስና ለብዙ አመት የተቀመጠችዉ የልጆቿን ሁለገብ ችሎታን ባለማወቅ ሆነ በሌሎች የውድድር ዘርፎች ልምድን እናን ስልጠናን አለማካበት ይሁን ሌላም ነገር ይህ ነዉ ለማለት ባልችልም: ዘንድሮ በአራት መቶ መሰናክል እና በጦር ውርወራ ወር ቅን በጇ ስታስገባ ለአፍሪቃኖች ለሌሎችም ለማይታሰቡ ውድድሮች በሩን ማንኳኳት እንደሚቻልና ለሌላዉ አለማት የልብ ትርታን የጨመረበት ጊዜ ነበር።

አፍሪቃ የኦሎንፒክ ድልን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታይ ያደረጋት በጀግኖቹ የኢትዮጰያ አትሌቶች በነበቂላ እና ማሞ ነበርና አትሌቶቿ ተሳትፎአቸዉ እና ድሎቿ በማራቶን፣ በአስር ሺህ እና በአምስት ሺህ የተወሰነ ነበር። ከዘመኖች መሸጋገር በኋላ እንሆ ዛሬ በማራቶን፣ አስር ሺህ፣ አምስት ሺህ፣ ሶስት ሺህ፣ አንድ ሺህ አምስት መቶ፣ ስምንት መቶ፣ ሶስት ሺህ እና አራት መቶ መሰናክል እንዲሁም በጦር ውርወራ የወረቅ ባለቤት ሆናለች። እንግዲህ በትራኩ የቀራት ሁለት እና የመቶ ሜትር ሩጫ እና የዱላ ቅብብል ብቻ ሲሆን ትኩረት ከተሰጠበት የመሬት እና የከፍታ ዝላዩ እንዲሁም ሌሎች ውድድሮች በአፍሪቃ ጉሮሮ ውስጥ ማለፍ እማይችሉበት ምክንያት የለም።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በሜዳልያ ጠረጴዛ አፍሪቃ በልጆቿ ኬንያ እና ኢትዮጰያ የአንድ እና የአምስተኛ ደረጃን መያዝና ኬንያ እነ አሜሪካን፣ ቻይናን፣ እንግሊዝን አስከትላ በአንደኛ ደረጃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀምጣ ማየት እጅጉን የሚያኮራ እና ለሚቀጥለዉ ትዉልድ አበረታችና ለአሁጉሯ አነቃቂ መድሃኒት ነዉ።
የኬንያን አትሌቶች ከታላቅ አክብሮት ጋራ እጅ ነስተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *