መደበኛ ያልሆነ

የቪዛ ጉዳይ በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካ ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ መስጠት ጀምራለች
ኢትዮጵያ ከጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት ህዝቦች በቦሌ አለምዓቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች።
የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ የአገልግሎቱን መጀመር በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለህብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች እንዲሁም ለህብረቱ ኮሚሽንና የተ.መ.ድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮችና ባልደረቦች ገለፃ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የአፍሪካ አገራትን መቀላቀሏ የህብረቱን የነፃ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ፍሰትና ትስስሮችን የሚያሰፋና የአህጉራዊ ውህደት አጀንዳውን ተፈፃሚነት የሚያፋጥን እንደሚሆንም ገልጸዋል።
አህጉራዊ የአየር ትራንስፖርትና የመሰረተ ልማት ትስስሮች እንዲፋጠኑ እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቱና ሴቶች የአገር ፕሬዝዳንትነት፣ የካቢኔ ሹምነት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊነቶችን በስፋት እንዲይዙ ማድረጋቸውም የህብረቱ ቁልፍ አጀንዳዎች የሆኑትን አህጉራዊ የወጣትና ጾታዊ ተሳትፎ የማሳደግ አጀንዳዎች ለማሳካት በሞዴልነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ አገራችን አገልግሎቱን መጀመሯ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲናነቷን እንደሚያሳድገው ገልጸው ሌሎች የህብረቱ አባል አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ለብስራት ሬድዮ በላከው መግለጫ መሰረት የህብረቱ አባል አገራት ተወካዮች በበኩላቸው ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው ቀሪ አባል አገራትም ተመሳሳይ መንገድ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከመላው አለም ወደ አገራችን ለቱሪዝም መምጣት ለሚፈልጉ ሁሉ በኢንተርኔት ማመልከቻ አቅርበው ሲፈቀድላቸው ተገቢውን ክፍያ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ሲፈጽሙ የመዳረሻ ቪዛ የሚያገኙበትን አሰራር መጀመሯ የሚታወስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *