መደበኛ ያልሆነ

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ

የአዲስ አበባን ንግድ ቢሮ “ወደ መደበኛ የንግድ ስርዓት የማስገባቸው፣የጎዳና ነጋዴዎች፤የከተማዋን የኑሮ ውድነት እንደሚያቃልሉ ተስፋ አለኝ” ብሏል፡፡
በቅርቡ ወደ መደበኛ የንግድ ስርዓት የሚያስገባቸው፤የጎዳና ነጋዴዎች፤የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው፤የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያለውን እምነት ገልጧል፡፡ ስርዓት እየተዘጋጀለት ያለው የጎዳና ንግድ፤የስራ ዕድልን በመፍጠር እና ፍትሀዊ የንግድ ውድድርን በማስፈን፤ለኑሮ ውድነት መቀነስ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ለብስራት የተናገሩት፤የንግድ ቢሮ ም/ሀላፊ አቶ አሰግደው ሀ/ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤በጥቅሉ በዚህ ዓመት፤በህጋዊ መንገድ የሚሰማሩ የጎዳና ነጋዴዎች፤በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ፤የታሸጉ ምግቦችን፣መጠጦችን፣አልባሳትን እና ጫማዎችን በማቅረብ፤የገበያ ማረጋጋት ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም፤ለኑሮ ውድነት ቀዳሚ ምክንያት የሆነው የሸቀጦች ዋጋ መናር በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀንስ እና ለዜጎችም የአማራጭ ምርቶችን ብዛት እንደሚጨምር፤አቶ አሰግደው ለብስራት ተናግረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ካለፈው መጋቢት ወር አንስቶ በተከናወነ ምዝገባ፤24 ሺህ 778 መደበኛ ያልሆኑ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ስለመኖራቸው የታወቀ ሲሆን፤ከእነዚህ ውስጥ 6ሺህ 502 የሚሆኑትን ቢሮው በመመዝገብ እና የንግድ መለያ ቁጥር በመስጠት ወደ መደበኛ ንግድ አስገብቷል፡፡ እስከ ጥቅምት 30 በሚቆየው የምዝገባ ጊዜም፤ይመዘገባሉ ተብለው የሚጠበቁትን ጨምሮ፤ በጥቅሉ 35ሺ የጎዳና ነጋዴዎችን፤በዚህ ዓመት ወደ መደበኛ የንግድ ስርዓት ለማስገባት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አቅዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *