መደበኛ ያልሆነ

ከሰሞኑ እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፤ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል ተባለ፡፡

በኢትዮጵያ አንዳንድ አከባቢዎች ካለፉት 2 ሳምንታት አንስቶ እየጣለ የሚገኘው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፤ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ያስታወቀው ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ነው፡፡ የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱል-ከሪም ለብስራት እንደተናገሩት፤በመጪዎቹ አስር ቀናት ደረቃማ የአየር ሁኔታ በአመዛኝ እንደሚኖር የሚጠበቅ ቢሆንም፤በጥቂት ሰሜናዊ እና ደቡባዊ አጋማሽ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከመኖሩም ባሻገር፤በደቡባዊው አጋማሽ አከባቢዎች ላይ ከበድ ያለ ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም፤ሰብሎችን የመሰብሰብ ስራው አዳጋች ሊሆን እንደሚችል፤የኤጀንሲው ትንበያ ማመላከቱን ከአቶ አህመዲን ሰምተናል፡፡ ወቅቱን ካልጠበቀው ዝናብ በተጨማሪ፤በአንዳንድ ሰሜን፣ የሰሜን ምስራቅ፣ የምስራቅ፡ የመካከለኛው እና የደቡብ ደጋማ አከባቢዎች፤የሌሊቱ እና የማለዳው ቅዝቃዜ ጠንከር ብሎ እንደሚቀጥልም፤በትንበያው ተገልጧል፡፡ ከዚህ ቀደም፤ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚፈጥረው እርጥበት፤ሙሉ በሙሉ በደረሱ እና በመሰብሰብ ሂደት ላይ በሚገኙ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል፤ብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ያለውን ስጋት ገልፆ እንደነበር ብስራት ሬዲዮ የነገራችሁ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *