የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ መታየት የጀመረው የእርቅ፣ ሰላምና ትብብር ጥረት በጣም የሚደነቅ መሆኑንና ይህም ዘላቂ እንዲሆን የአለምዓቀፉ ማህበረሰብ ትርጉም ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀ።
የህብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞጌሪኒ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ደረጃ የተጀመረውን ተከታታይ ምክክርና በቅርቡ በባህርዳር ከተማ የተደረሰውን የሶስትዮሽ መግባባት አድንቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ እንዲነሳ መወሰኑ የተጀመረውን የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ሰላምና የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፋጠን ይረዳዋልም ብለዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ የአውሮፓ ህብረት ለተጀመረው የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ትብብር እንዲሳካና ዘላቂነት እንዲኖረው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
አለምዓቀፉ ማህበረሰብም ለዚህ ታሪካዊና ለሌሎች አርአያ ለሆነ ጥረት ሰፊ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ለብስራት ሬድዮ በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡