መደበኛ ያልሆነ

በእነ አብዲ ኢሌ የምርመራ መዝገብ ላይ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በኢትዮ-ሶማሌ ክልል በተከሰተው ሁከትና ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት በተፈጸመው ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ ሲሉ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት እነ አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)፣ራህማ መሀመድ፣አብራዛቅ ሳኒ እና ኮሚሽነር  ፈርሃን ጣሂር ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ የፌዴራል መርማሪ ፓሊስ ከአሁን በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የነበረውን የአሰራር ችግር በመቃወማቸው ምክንያት 200 የሚሆኑ ዜጎችን በጸረ-ሰላም ሃይል በመፈረጅ ተገድለው በጅምላ እንደ ተቀበሩ አዲስ የምርመራ ቡድን መሰማራቱን  ተናግሯል ብለዋል፡፡

101 የሚሆኑ ሰነድ ማስረጃዎችን ወደ ህጋዊ ትርጉም ጽ/ቤት መላኩን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስቲያን 300 ሚሊዮን እና በክራውን ሆቴል ደግሞ 42 ሚሊዮን የሚሆን ጉዳት እንደደረሰ ማስረጃ መጠየቁን እንዲሁም  ሌሎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በማስረዳት ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ለችሎቱ አመልክቷል ፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆችም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅ መቆየቱ ተገቢ አለመሆኑን በማስረዳት የተጀመረው አዲስ ምርመራም ከተጠርጣሪዎቹ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ለችሎቱ ገልፀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የተፈጸመው ወንጀል ከባድና ወስብስብ መሆኑን እና የተሰራውን ስራ ግምት ውስጥ በማስገባት ለህዳር 27 ቀን 2011ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲሉ አቶ ዝናቡ ቱኑ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

ቤተልሄም እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *