ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሲቪል አቭየሽን ባለስልጣን ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የነበሩት አቶ ተፈራ መኮንን የአፍሪካ ሲቪል አቭየሽን ዋና ጸሀፊ በመሆን ተመርጠዋል፡፡
ድርጅቱን ለመምራት ኢትዮጵያ ያቀረበችው ዕጩ መመረጡ ለቀጠናው የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይሆንም ተብሏል፡፡
ድርጅቱ በዛምቢያ ሊቪንግስተን ውስጥ ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ በዕጩነት ያቀረበቻቸውን አቶ ተፈራ መኮንን በመምረጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደስታውን ገልፅዋል፡፡
በቅርቡ በተጠናቀቀው 11ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጉባኤ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከአፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር በመገናኘት ግለሰቡ ብቸኛ ተመራጭ እንዲሆኑ የማግባባት ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ፣ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ለኢትዮጵያ ላሳዩት የመተማመን መንፈስ እና ላሳዩት ወገንተኝነት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አፍሪካ የሲቪል አቭየሽን እ.ኤ.አ. በ1964 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ እንድነት ድርጅት ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ስራውን የጀመረው በ1969 ነው፡፡
የሲቪል አቭየሽኑ መቀመጫም በሴኔጋል ዳካር ከተማ ነው፡፡
አቶ ተፈራ መኮንን በአቭየሽን ስራ የ37 ዓመት ልምድ አካብተዋል፡፡ በኬኒያ ናይሮቢ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቬየሽን ድርጅት ፕሮጀክት ማኔጀር በመሆን እንዲሁም በአፍሪካ የሲቪል አቪየሽን ትራንስፖርት ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡
ብስራት ሬድዮ ከውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት በተላከለት መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ በመሆንም ለስምንት ዓመታት ያክል በካናዳ ሞንቴሪያል ሰርተዋል፡፡