በገቢዎች ሚኒስቴር በጉምሩክ ኮሚሽን ስር ባለዉ በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት 41 ሺ 693 የአሜሪካ ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለማስወጣት የሞከሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በገቢዎች ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ በተለይም ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል፡፡
አረጋዊ ኪዱ፣ጽጌ ብርሃኔ እና ክብሮም ገብረ ሚካኤል የተባሉ ሲሆን ታህሳስ 10/2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ በቶጎ ጫሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በጉምሩክ ሰራተኞች ሊያዙ ችለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በጉምሩክ ኮሚሽን የጋላፊ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በቀን ማክሰኞ እለት ከቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ 40 ኪ.ግ የሚመዝን የካናቢስ ዕጽን በላስቲክ ተጠቅልሎ በተሸከርካሪ በመጫን ወደ ጅቡቲ ይዞ ሊወጣ ሲል በጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሊያዝ ተችሏል፡፡
የመኪናው አሽከርካሪ ዕቁባይሚካኤል ገ/ትንሣኤ በቁጥጥር ስር ውሎ አስፈላጊው የማጣራት ስራ እየተሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡
ይሄን መሰል ህገ-ወጥ ድርጊት ለመከላከል መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝና ህብረተሰቡም በቀጣይ ህገ-ወጦችን በንቃት በመከታተል ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አቶ አዲሱ ጨምረው ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል፡፡
ሚኪያስ ፀጋዬ