መደበኛ ያልሆነ

ሚያዝያ 16፣2012-ቁጥራቸው ስድስት የሆኑ ግለሰቦችን ሰብስቦ ጫት ሲያስቅም እና ሺሻ እያስጨሰ የተገኘው ተከሳሽ በገንዘብ ተቀጣ

የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ደንብ የተከለከሉ ተግባራትን ሲፈፅም የተገኘው ተከሳሽ በገንዘብ ተቀጥቷል፡፡

ተከሳሽ መለሰ ንዳው ሸረፍ ሚያዝያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታ “ቁልፍ ተራ” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ቁጥራቸው ስድስት የሆኑ ግለሰቦችን ሰብስቦ ጫት ሲያስቅም እና ሺሻ እያስጨሰ የተገኘ በመሆኑ በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበታል፡፡

የፌደራሉ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ ወንጀል ችሎት በአፋጣኝ እንዲታይ በቀረበ መዝገብ (RTD) ተከሳሽን አስቀርቦ በተመሰረተበት ክስ ላይ ቃሉን አድምጧል፡፡

ተከሳሽ “ በተመሰረተብኝ ክስ አዎ ጥፋተኛ ነኝ ድርጊቱንም ፈፅሜአለሁ ተፀፅቻለሁ የተከበረው ፍርድ ቤትም አስተያየት ያድርግልኝ ” ሲል ጥፋቱን በማመን የቅጣት ውሰኔው እንዲቀልለት ጠይቋል፡፡

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ከዚህ በፊት ሪከርድ የሌለብ እና ጥፋቱን ያመነ እና የተፀፀተ በመሆኑ ሁለት የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ ፤ ተከሳሽን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል በሚል ተከሳሽ በአምስት ሺ ብር እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *