
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ 23 ተከሳሾችን ይዞ ማስቀጣቱን አስታወቀ፤ተከሳሾቹ በልዩ ልዩ ጥፋቶች ላይ መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡
የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ ታረቀኝ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገጉ ጉዳዮችን ጥሰው የተገኙ 852 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል 789 ያህሉ በክ/ከተማው በተዋቀረው ግብረ ኃይል በምክርና በተግሳፅ እንደታለፉ ገልፀዋል፡፡
ተከሳሾቹ ሺሻ በማስጨስ ፣ ጫት በማስቃም ፣ ኢንተርኔትና ቪዲዮ ቤት ውስጥ ተሰብስቦ
መገኘት ፣ ፑል ቤት መሰባሰብ ፣ በቁማር ቤቶች በመገኘት ፣ መጠጥ መሸጥና ተሰብስቦ መገኘት ፣ ርቀትን ሳይጠብቁ መገኘትና የመሳሰሉት ጥፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመኪና ውስጥ ሳይቀር ተሰባስበው አልኮል መጠጥ ሲጠጡ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር የዋሉም እንዳሉ ገልፀዋል፡፡
ፖሊስ በተለይም ከአዋጁ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ጥፋቶችን በአጥፊዎች ላይ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥ ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቦሌ ምድብና ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ጋር እየሰራ መሆኑን የነገሩን የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ፅ/ቤት ም/ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ቢሻው ገልጸዋል።
እስካሁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈፀም ረገድ በ23 ተከሳሾች ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥባቸውና እንዲቀጡ መደረጉን የገለፁት ሃላፊዋ ፤ ቀሪ 29 ተከሳሾች ጉዳያቸውም እየታየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡