መደበኛ ያልሆነ

ሚያዝያ 26፣2012-በድሬደዋ አስተዳደር በሰኔና ሐምሌ መጀመሪያ የኮሮና ወረርሽኝ ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋት መኖሩ ተገለፀ

የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ የነበሩ 6ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከቫይረሱ ማገገማቸውን ጠቁሟል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ከጅቡቲ ተመላሽ ሆነው በማዕከላት የሚገኙና የህክምና ክትትል እና ናሙና ምርመራ እየተደረገላቸው ከሚገኙ ዜጎች መካከል 151 ሰዎች ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን በአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በቤት ለቤት ልየታ ከ60ሺ በላይ ቤቶችን ለማዳረስ መቻሉንና ከበሽታው ጋር ተቀራራቢ ምልክት ያሳዩ 178 ሰዎች ተለይተው በባለሙያ የህክምና ክትትል ተደርጎላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ ይሁንና በትናንትናው እለት በጅግጅጋ ከተማ 4 ሰዎች በተጨማሪነት በቫይረሱ መያዛቸው ለአስተዳደሯ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድልን ያሰፋል ብለዋል፡፡

አክለውም በቀጣይ ክረምት መግቢያ ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመሪያ ፤ በከተማዋ ሊከሰቱ ከሚችሉት ደንጊ ፣ ችኩንጉኒያና ወባ በሽታ ጋር ተያይዞ በሽታው ሊስፋፋ ይችላል በመሆኑም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

አካባቢን ማፅዳት ረግረግ ቦታዎችን በማድረቅ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ የቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡

በድሬደዋ አስተዳደር በሽታው እንዳለ ከታወቀ ጀምሮ 901 ናሙናዎች መላካቸው የተጠቆመ ሲሆን በአስተዳደሩ በአሁኑ ሰአት በቫይረሱ ተይዘው ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ 6 ሰዎችም ሙሉ ለሙሉ ከቫይረሱ ማገገማቸውንም ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *