መደበኛ ያልሆነ

ሚያዝያ 26፣2012-4 ሰዎች በደራሽ ውሃ ተወስደው ህይወታቸው አለፈ

ደቡብ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ትናንት በጣለው ከባድ ዝናብ 4 ሰዎች በደራሽ ውሃ ተወስደው ህይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የገዜ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የመረጃ ኢንተለጀንሲ ደጋፊ የስራ ሂደት አስተባባሪ ሳጅን አበባው አስናቀ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የተከሰተው በትናንትናው ዕለት በወረዳው አላ ጋልፃ በተባለ ቀበሌ ነው።

በአካባቢው የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ባልና ሚስትን ጨምሮ 4 ሰዎች በደራሽ ውሃ ተወስደው ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።

ሟቾቹ በአካባቢው ለቅሶ ለመድረስ ሚቶ የተሰኘውን ወንዝ በመሻገር ላይ እያሉ በደራሽ ውሃ እንደተወሰዱ ሳጅን አበባው ጠቁመዋል።

በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ 3 ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በሳውላ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በተከታታይ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ተጨማሪ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ሳጅን አበባው አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *