መደበኛ ያልሆነ

ሚያዝያ 30፣2012-አቶ በረከት ስምዖን የ6 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ፍርድ ቤቱ በአቶ በረከት ስምኦን ላይ ስድስት ዓመት እና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የ8 ዓመት የእስር ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ምንም እንኳን ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው እንደተጠበቀ ቢሆንም ባለፉት 15 ወራት በሕግ ጥላ ስር አርፈው ጉዳያቸው ሲታይ የነበረው የሀገሪቱ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳይ ዛሬ መቋጫ አግኝቷል፡፡

በአቶ በረከት ስምኦን እና በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥራን በማያመች መንገድ መምራት የሙስና ወንጀል ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ክርክር ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ፍርድ ቤቱ የከሳሽንና የተከሳሾችን ክርክር ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት መዝገቡን መርምሮ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳን ጥፋተኛ ብሏል፡፡

ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም የዋለው ችሎት ደግሞ በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል የቅጣት ውሳኔ አስተያየትን አዳምጦ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም መቀጠሩን መዘገባችን ይታወቃል፡፡

ዛሬ ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት በፊት የዋለው ችሎትም በ1ኛ እና 2ኛ የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በተባሉት በ1ኛ ተከሳሽ አቶ በረከት ስምኦን ላይ የስድስት ዓመት እስር እና የ10 ሺህ ብር የቅጣ ውሳኔ አስተላለፏል፡፡

በ1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ የክስ መዝገቦች ላይ ጥፋተኛ በተባሉት 2ኛ ተከሳሽ አቶ ታደሰ ካሳ ላይ ደግሞ የ8 ዓመት የእስር ቅጣትና የ15 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ ተበይኗል፡፡

ተከሳሾች ይግባኝ የማለት መብት እንዳላቸው የገለፀው ችሎቱ ፍርዱ በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ይሰላልም ተብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *