መደበኛ ያልሆነ

ግንቦት 12፤2012- በአንድ ሳምንት ውስጥ ከተፈቀደላቸው ቀን ውጭ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ፤ ከሶስት መቶ በላይ ኮድ 2 አሸከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ለማስፈፀም የወጣውን የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም መመሪያ ተከትሎ በተደረገ ቁጥጥር ከተፈቀደላቸው ቀን ውጭ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ከሶስት መቶ በላይ በሚሆኑ ኮድ 2 አሸከርካሪዎች ላይ ነው እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለብስራት ሬድዮ እንደገለፁት ፤ ከግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ ግንቦት 8 ድረስ ባሉት ቀናት ማዕከልን ጨምሮ በ10ሩም ክፍለ ከተማ የተደረገ ቁጥጥርን መሰረት ተደርጎ ነው በህጉ አግባብ አስፈላጊው እርምጃ የተወሰደው፡፡
በሰሌዳ ቁጥራቸው መሰረት በማይንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ጨምረው ነግረውናል፡፡
ከሚያዚያ 09 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሰሌዳቸው የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ ወይም ዜሮ የሆኑት ማክሰኞ ፣ ሀሙስ ፣ ቅዳሜ ፣ መንቀሳቀስ እንደሚችሉና ሰኞ ፣ እሮብ እና አርብ ደግሞ የሰሌዳቸው የመጨረሻ ቁጥር ጎዶሎ የሆኑ ኮድ 2 ተሸከርካሪዎች እንዲያሽከረክሩ ሲፈቀድ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን እሁድ ለሁሉም ተሸከርካሪዎች ነፃ ቀን መሆኑ በመመሪያው መደንገጉ የሚታወስ ነው፡፡

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *