መደበኛ ያልሆነ

ግንቦት 14፤2012-የደቡብ ክልል በኮሮና ቫይረስ ከተጠቃ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው 381ሰዎችን በመለየት ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ፤ በክልሉ 381 ንክኪ ያላቸው ሰዎችን በመያዝ ማቆያ ውስጥ በማስገባት አስፈላጊው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት 805 ዜጎች ኳራንታይን ውስጥ እንደሚገኙና 106 ሰዎች ደግሞ በበሽታው የተጠረጠሩ በመሆኑ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ቤቶች ላይ አሰሳ የተደረገ ሲሆን ለ6 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች የሙቀት ልኬት ማካሄድ ተችሏል፡፡

በክልሉ ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻር አሁን እየተካሄደ ያለውን የክትትል ስራ ማጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

በየቀኑ የቫረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ሪፖርት እየተደረገ ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የህግ ጥሰት የፈጸሙ144 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ7ሺ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ከ 6 ሺ በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይም ከምክር ጀምሮ ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ መውሰድ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የ1441ኛውን የኢደል ፈጥር በአል በማስመልከት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢደል ፈጥር በዓል ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአደባባይ ባይከበርም ሙስሊሙ ማህበረሰብ እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ወቅቱን በጥንቃቄ ማለፍ ይገባል ብለዋል፡፡

በሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *