መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 18፤2013-የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ከሚገኙ ምርጥ አስር ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ መመደቡ ተገለጸ!

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባደረጋቸው ችግር ፈቺ የምርምር ተግባራት በዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ መዳቢ አካላት በአፍሪካ ከሚገኙ ምርጥ አስር ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ መመደቡን ገልጸዋል፡፡ዩኒቨርሲቲው ለዚህ የበቃው በምርምር ውጤቶችና በዩኒቨርሲቲው የሚታተሙ ህትመቶች ለሌሎች ተመራማሪዎች እና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባላቸው የችግር ፈቺነት አቅም መሆኑን አመልክተዋል።

የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚያሳትመው ህትመት ብዛት እንደሚበልጥ ያመለከቱት ፕሬዝደንቱ ፤ በህትመቶች ተጠቃሽነት ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚበልጥ አስታውቀዋል።ይህ የሆነው በዩኒቨርሲቲው የሚደረጉ ጥናቶች እና ምርምሮች ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ በበለጠ ለህብረተሰባችን ፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሊጠቅሙ የሚችሉ ጥናቶች እንደሆኑ በደረጃ መዳቢ አካላት እውቅና በማግኘቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።ሌሎች የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እዚህ ውድድር ውስጥ ገብተው እንደነበር የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ፤ ነገር ግን በሀገራችን ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የአዲስ አበባ እና የጎንደር የኒቨርሲቲ ብቻ ከ1 ሺ 500 ምርጥ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ 49ኛ ደረጃ ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው በ26 ወሳኝ የምርምር ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ በመስጠት በሀገሪቱ ፣ በአህጉሪቱ እና በዓለም ችግር ላይ ሁነኛ መፍትሔ ለመፈለግ እየተጋ ያለ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ካሉ አስር ምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ከመሆን ባለፈም በህትመት ስኬታማነት ደግሞ በአፍሪካ ካሉ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው ብለዋል።እንደ ፕሬዚደንቱ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር ፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ለአለፉት ሰባ ዓመታት በርካታ ስራዎችን ሲከናውን ቆይቷል።

ዩኒቨርሲቲው በ1950 ዓ.ም 33 ተማሪዎች እና 7 አስተማሪዎች ትምህርት እና ምርምር በማካሄድ የጀመረው መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ሰዓት ከ3 ሺ በላይ መምህራን ፣ 5 ሺ የሚሆኑ የአስተዳደር ሰራተኞች ፣ 1 ሺ 200 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ፣ ከ46 ሺ በላይ ተማሪዎች ፣ 12 ኮሌጆች እና 10 የምርምር ተቋማትን ይዞ የሀገሪቱን የልማት አቅጣጫ ተከትሎ እየሰራ ያለ ትልቅ ተቋም መሆኑን አመልክተዋል።የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ልዩ የሚያደርገው በእድሜ ትንሹ እና ብቸኛው በቅኝ ገዥዎች ያልተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት ፕሬዚደንቱ ፤ ይሁን እንጂ እድሜ ሳይገድበው እድሜ ጠገብ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ቀድሞ መቆም የቻለ መሆኑን አስታውቀዋል።ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ በሁለንተናዊ መልኩ ከአምስት ዓመት ወዲህ እያሳየ ያለው መሻሻል ወደ ፊት በአፍሪካ ብሎም በዓለም ከሚገኙ ዩኒቨርሰቲዎች ተርታ ቀዳሚ ሊያደርገው እንደሚችልም እምነታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *