መደበኛ ያልሆነ

ጥር 6፤2013-በትግራይ ክልል የደረሱ ዘረፋዎች፣ የሴቶች መደፈር፣ የንብረት ውድመት እና ግድያዎችን ገለልተኛ በሆነ አካል ባስቸኳይ እንዲጣራ ኢዜማ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በወቅታዊ ጉዳዮች እና በምርጫ 2013 ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የ2013 ሀገራዊ ምርጫ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታ ወደ የተሻለ የተረጋጋ ሀገራዊ ሁኔታ የመቀየርና ፣ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊና ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው እንደሚያምን ኢዜማ ገልጿል፡፡

በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች መሪዎቻቸው እና አባሎቻቸው በሕግ ጥላ ስር ከመሆናቸው የተነሳ ፣ የነዚህ ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ አለመሳተፍ ምርጫው ያለው አጠቃላይ ፋይዳ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል በሚል ፓርቲው ስጋቱን አስቀምጧል።

በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙ የፓርቲ አመራሮች የሁሉም ዜጋ ሕገ መንግሥታዊ መብት የሆነውን የተፋጠነ ፍትህ ሊያገኙ ይገባል ብሎ እንደሚያምንም ገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል እየተከሰቱ የሚገኙ ሥርዓት አልበኝነቶችን ለመቆጣጠር የፌደራል መንግሥት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በፍጥነት የፀጥታ መዋቅር ማቋቋም እና አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል።

በክልሉ ዜጎች ላይ የደረሱ ዘረፋዎች፣ የሴቶች መደፈር፣ የንብረት ውድመት እና ግድያዎችን ገለልተኛ በሆነ አካል ባስቸኳይ እንዲጣራ፣ ሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ እንዲሁም የመገናኛ ዘዴዎች መልሶ አገልግሎት እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራም ኢዜማ ጠይቋል፡፡

መንግሥት በክልሉ ከወሰደው እርምጃ ጋር ተያይዞ የሌላ ሀገር ወታደሮች ጣልቃ ገብነት ከነበረ ይህንኑ በግልፅ እንዲያስረዳ እና እነዚህ ወታደሮች አሁንም በሀገራችን ድንበር ክልል ውስጥ የሚገኙ ከሆነ መቼ እንደሚወጡ ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን።

በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ማንነትን ማዕከል ያደረግ ጥቃት አሰቃቂነት እና ተደጋጋሚነት ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ለጉዳዩ የሚመጥን ትኩረት ከፌደራል መንግሥት እና ከፀጥታ መዋቅሮች እንዲሰጥ እና ንፁሃን ላይ የሚደርሰው ግፍን እንዲያስቆሙም ኢዜማ ጠይቋል።

በምእራብ ወለጋ በየጊዜው ታጣቂዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ እያደረሱት ያለው ተደጋጋሚና አሰቃቂ ጥቃት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ቡድን ችግር ወደተፈጠረባቸው አካባቢዎች እንደሚልክና ፣ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በመመርመር እና ነዋሪዎችን በማረጋገር ችግሮቹን በተመለከተ የሚደርስበትን ድምዳሜ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።

ሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *