መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 3፤2013-የግብር ስርአትን ቀልጣፋ የሚያደርግ ስምምነት ተፈረመ

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ስርአቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከኢንፎርሚሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከአራት የግል ባንኮች ጋር ተፈራርሟል፡፡

በየገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ተገዥነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ስምምነቱ ከአዲስ አበባ ዉጪ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ግብር ከፋዮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል በኤሌክትሮኒክስ የታክስ ስርአትን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በማስተሳሰር ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ የግል ባንኮች ወደዚህ ስርአት እንዲቀላቀሉ መደረጉ የበለጠ አሰራሩ ለግብር ከፋዩም ሆነ ለግብር ሰብሳቢው አካል ምቹ ከማድረጉም ባሻገር ገቢን በብቃትና በወቅቱ ለመሰብሰብ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛዉ በበኩላቸው ግብር ከፋዮች በየትኛውም ቦታ ሆነው ግብራቸውን በባንክ ሲከፍሉ የመረጃ ደህንነት መጠበቅ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

አያይዘውም በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት አላማዎችን በማክሸፍ አሰራሩን የበለጠ ዉጤታማ ለማድረግ የተጣለባቸውን ሃገራዊ ሃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሃስ ሚሊዮን በበኩላቸው በአሰራር ስርአቱ በርካታ ዉጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልፀው ለበለጠ ውጤታማነት ደግሞ የግል ባንኮች ወደዚህ ስርአት እንዲገቡ መደረጋቸው አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *