
የሄይቲ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሄይቲ ስደተኞች ወደሀገራቸዉ መመለስን በመቃወም ሥራቸዉን ለቀዋል፡፡ዩናይትድ ስቴትስ ስደተኞቹን የታጠቁ ወንበዴዎች ወደሚቆጣጠሩባት ሀገር ለመላክ መወሰኗን በመቃወም ዳንኤል ፎኦት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸዉን አስገብተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አሜሪካ ስደተኞችን ከቴክሳስ ድንበር ከተማ መመለስ ጀምራለች፡፡ 13,000 የሚሆኑ ስደተኞች በ37 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሙቀት መጠን በጊዜያዊ ካምፕ በቴክሳስ ድንበር አቅራቢያ ተሰብስበዉ ነበር፡፡
የአካባቢው ባለሥልጣናት ምግብና በቂ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ሲያቀርቡላቸዉ ቆይተዋል፡፡በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ዉስጥ አብዛኛዎቹ የሄይቲ ስደተኞች ይሁኑ እንጂ ከኩባ ፣ ፔሩ ፣ ቬንዙዌላ እና ኒካራጓይ የመጡ ስደተኞች አሉበት፡፡
ከእሁድ አንስቶ አሜሪካ በሜክሲኮ ድንበር ላይ ከሚገኘው የቴክሳስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ 1 ሺህ 401 ስደተኞችን ወደ ሄይቲ መልሳለች። የተባረሩ ስደተኞችን የጫኑ አዉሮፕላኖች ሄይቲ ዋና ከተማ ፓርት ኤ ፕሪንስ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ሁከት መነሳቱ ይታወሳል፡፡
በሚኪያስ ጸጋዬ