
በሳውዲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በተመለከተ መንግስት ምንም እየሰራ አለመሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መነገሩ አግባብ አለመሆኑ ተገለፀ❗️
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫቸውን ሰጥተዋል።
በመግለጫውም በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ከተሰሩ ስራዎች በይበልጥ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 76ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፎ መደረጉንና ፤ በጉባኤው ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ቡድን መሳተፏን አስታውሰዋል።
በውይይቱም በህዳሴው ግድብ እና ኢትዮ ሱዳን ግንኙነት እንዲሁም በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታና ለተጎጂዎች ተደራሽ በሚሆኑ ድጋፎች ዙሪያ የተለያዩ ነጥቦች መነሳታቸንው ተናግረዋል። በኮቪድ ወረርሽኝ ዙሪያ የበለጸጉ ሃገራት ያላቸው አስተዋጸኦ ምን መሆን እንዳለበት ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሰፊ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።
በዋናነትም በመልቲላተራሊዝም ወይም አካታች አሰራር ላይ ኢትዮጵያ የማንም ሃገራትን መንካት እንደማትፈልግ ፤ ይሁንና ግን በውስጥ ጉዳዮችዋ እየተነዘነዘች መሆኑ ልክ አለመሆኑ መነሳቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ስራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አቶ ደመቀ መናገራቸውን አምባሳደሩ መግለፃቸውን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ረገድ ዜጎችን ከተለያዩ ሃገራት የማስመለስ ስራ እየተከናወነ ሲሆን ከሪያድ 794 ፣ ከጅዳ 892 ፣ ከየመን 357 ዜጎችን ማስመለስ ተችሏል።
ይሁንና ግን በሳውዲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በተመለከተ መንግስት ምንም እየሰራ አለመሆኑንና ጉዳዩን እንደረሳው ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተነገረ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።
ቤቴልሄም እሸቱ