መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 1፤2014-የሰአት እላፊ ገደቡ ባለበት እንደሚቀጥል የደሴ ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፀጥታ ምክር ቤት የደሴ ከተማ ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም ካሁን በፊት ያወጣው የሰአት እላፊ ገደብ ባለበት እንዲቀጥል እና ተጨማሪ ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል ከብስራት ሬድዮ ጋር ባደረጉት ማንኛውም የንግድ ድርጅትም ሆነ የሰዎች እንቅስቃሴ ከምሽቱ 2፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ በተጣለው የሰአት እላፊ ገደብ መሠረት ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ማህበረሰቡ ለፀጥታ ሃይሎች ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደሴ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ በመኖሩ ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ያልተፈቀዱ ስብሰባዎች እና ህገ-ወጥ ሰልፎች ማድረግ በጥብቅ ተከልክላል፡፡በከተማው ውስጥ ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትን ለፀጥታ ሃይሉ በመጠቆም እና በማስያዝ ማህበረሰቡ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል ጨምረዉ ማህበረሰቡ አካባቢዉን ተደራጅቶ በመጠበቅ ለፀጥታ ሃይሉ የሚያደርገዉን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ማንኛውም ሰው ከተፈቀደለት የፀጥታ ሃይል ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም ሆነ በመዝናኛ ቦታ ይዞ መገኘት ተከልክሏል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያን እና የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረገ ሲሆን ወጣቱ ተደራጅቶ አካባቢውን ለመጠበቅ እያደረገ ላለዉ ርብርብ ከንቲባዉ አቶ አበበ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *