
በሰኔ 14ቱ ሀገራዊ ምርጫ ወቅት አንዲት የፖለቲካ ፓርቲ እጩን ጨምሮ በሰባት ሴቶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ደርሷል ❗️
የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ፤ በኢትዮጵያ በሰኔ ወር በተከናወነው 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሴቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶችን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አዉጥቷል።
ማህበሩ ለብስራት ራዲዮ በላከዉ መረጃ እንደተመላከተዉ ፤ በሴቶች ላይ የተፈፀሙ ዛቻ አልያም ማስፈራሪያ በተመለከተ 41 ክስተቶችን ታዝበዋል።
“ከምርታማ የሴፍቲኔት ፕሮግራም እንሰርዛችኋለን” በማለትም ፤ የአካባቢ ሹማምንቶች ሴት መራጮችን እነርሱ በሚፈልጉት ሁኔታ ድምፅ እንዲሰጡ ጫና በመፍጠር ሴት መራጮችን ሲያስፈራሩ አንደነበር ተጠቅሷል።
በአማራ ፣ በኦሮሚያ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር አብዛኞቹ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ፤ በቤኒሻንጉል ፣ ጋምቤላ እና አዲስ አበባ ከተማ በተወሰነ መልኩ ችግሩ መስተዋሉን ማህበሩ አስታውቋል።
በተጨማሪም 7 ወሲባዊ ትንኮሳዎች በምርጫው ወቅት በሴቶች ላይ ደርሷል። በሴት መራጮች ላይ 3 ፣ ለመምረጥ በመመዝገብ ላይ በነበሩት 2 ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዲሁም የፓርቲ ደጋፊ ላይ 2 በድምሩ 7 ወሲባዊ ትንኮሳዎች በምርጫው ወቅት በሴቶች ላይ እንደደረሱ ሪፖርቱ አትቷል።
የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ታዛቢዎች ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና የአካባቢ መስተዳድር ተወካዮች ፤ የሴት መራጮችን ድምፅ ለማግኘት የተደረጉ ሙከራዎችን በሚመለከት 10 ክስተቶችን ማግኘቱን ብስራት ከሪፖርቱ ተመልክቷል።
በረከት ሞገስ