
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሀፊ እና በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ በቦታዉ መሾም የቻሉት የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ኮሊን ፓውል በ ኮቪድ የተነሳ ህይወታቸዉ ማለፉን ቤተሰቦቻቸዉ አስታዉቀዋል፡፡እ.ኤ.አ በ2005 የመንግሥት ሥልጣን የያዙት ባለ አራት ኮከብ ጄኔራል የነበሩት ፓውል በዛሬዉ ዕለት በ84 ዓመታቸዉ ዜና እረፍታቸዉ ተሰምቷል፡፡
ሙሉ በሙሉ ክትባት ወስደዉ እንደነበር ተገልጿል። በዋልተር ሪድ ብሔራዊ የህክምና ማዕከል እንክብካቤ ላደረጉልን ሠራተኞች ማመስገን እንፈልጋለን፤ አስደናቂ እና አፍቃሪ ባል ፣ አባት ፣ አያት እና ታላቅ አሜሪካዊ አጥተናል ሲሉ የፓውል ቤተሰብ አባላት ተናግረዋል።የተግባር ሰዉ በመባል የሚታወቁት ፓውል የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ አስተዳደር የውጭ ፖሊሲን ለአስርተ ዓመታት በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በበርሊን ግንብ መደርመስ ወቅት፣ በ1989 የአሜሪካ ፓናማ ወረራ ፣ በ1991 የባህረ የገልፍ ጦርነት ፣ በመስከረም 11 ጥቃት እና በውጤቱ የአሜሪካ አፍጋኒስታን ወረራ በ2003 በኢራቅ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ነበራቸዉ፡፡ከ 1987 እስከ 1989 ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
እ.ኤ.አ. በ2001 በትንሹ ቡሽ አስተዳደር ዉስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ፣ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ለመባል በቅተዋል፡፡ እርሳቸዉን በመከተል በባራክ ኦባማ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሀፊ በመሆን ኮንዶሊዛ ራይስ መሾማቸዉ አይዘነጋም፡፡
በስምኦን ደረጄ