
“አሸባሪው ህወሓት መሣሪያዎቹን ሲጨርስ ምላሱን መተኮስ ጀምሯል!” ያለው አገልግሎቱ፣ ሰሞኑን በደረሰበት ከባድ ምት ከተበታተነው ወራሪ ኃይል መካከል በጣት የሚቆጠረው በቦሩ ሜዳ አቅጣጫ በየወንዙ፣ በየጢሻው እና በየሸለቆው ተደብቆ ከርሞ እንደነበር ገልጿል።ለቀናት ከተደበቀ በኋላ ርሃብ እና ውኃ ጥም ሲከብደው የእሩምታ ተኩስ በመክፈት ከጉድጓድ እየወጣ የአካባቢውን ሕዝብ ለማደናገር ቢሆክርም አይጥ ከጉድጓዷ በራቀች ቁጥር እንደምትመታው፣ ይሄም የተቆረጠ አሸባሪ ወዲያው ተመትቷል ብሏል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት።
የተቆረጠው ኃይል ወደ ሲኦል እየተሸኘ ባለበት፣ በውስጥ ያሰረጓቸው ኃይሎች ጁንታው ወሎ ዩኒቨርስቲ አካባቢን እንደተቆጣጠረ በማስመል የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ እንደሚገኙም አስታውሷል።ጀግናው መከላከያ እና መላው የፀጥታ ኃይል እነዚህን ባንዳዎች በመልቀም ርምጃ እየወሰደ ነውም ብሏል።
ቦሩ ሜዳም ሆነ ከቦሩ ሜዳ ራቅ ያሉት አካባቢዎች በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት እጅ ላይ እንደሚገኙ አገልግሎቱ አረጋግጧል።ኅብረተሰቡ የሐሰተኛ ወሬ ፈጣሪዎችንም ሆነ አስተላላፊዎችን ለሕግ እያቀረበ አካባቢውን እና ቀዬውን አሁንም በንቃት እንዲጠብቅም አሳስቧል።የደሴ ከተማ ሕዝብ የሽብር ቡድኑን የሚያሸንፈው በፅናት እና በትግል ብቻ መሆኑን አስታውሶ፣ በወሬ የተገነባ ከተማ ስለሌለ፣ በወሬ የሚያዝ ከተማ አይኖርም! ሊኖርም አይችልም ሲል መልእክቱን ቋጭቷል።