
ሪፐብሊካኑ ግሌን ያንግኪን የቨርጂኒያ ገዥ ሆነው ተመረጡ
ሪፐብሊካኑ ግሌን ያንግኪን የቨርጂኒያ ገዥ ሆነዉ መመረጣቸዉን የአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን አስታዉቀዋል፡፡99% የመራጮች ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን ከዲሞክራት ቴሪ ማካውሊፍ በ2.1 ነጥብ በመብለጥ ግሌን ያንግኪን አሸንፈዋል፡፡
ምርጫው በጆ ባይደን አስተዳደር ላይ የተደረገ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ በሰፊው የተወሰደ ሲሆን፣ሽንፈቱ ለዲሞክራቶች አስፈሪ ሆኖ ተወስዷል፡፡ከአንድ አመት በፊት በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባይደን በቨርጂኒያ በ10 ነጥብ ልዩነት ማሸነፋቸዉ ይታወሳል፡፡ያንግኪን ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር የቨርጂኒያን ግዛት ለመለወጥ በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ቃል ገብተዋል።
እኛ የምንሰራው በእውነተኛ የሰዎች ጊዜ እንጂ በመንግስት ጊዜ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡የቨርጂኒያ የወቅቱ ዲሞክራቲክ ገዥ ራልፍ ኖርታም በቨርጂኒያ ግዛት ህግ መሰረት በተከታታይ የስልጣን ዘመን እንዲያገለግሉ ስለማይፈቅድ ለድጋሚ ምርጫ መወዳደር አልቻሉም፡፡የቀድሞ የአሜሪካ የባህር ኃይል አባል ሪፐብሊካኗ ዊንሶም ሲርስ፣ የቨርጂኒያ ግዛት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ሌተናል ገዥ ትሆናለች።
በተያያዘ መረጃ የቀድሞ የፖሊስ ካፒቴን ኤሪክ አዳምስ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ተደርገው የተመረጡ ሲሆን የዲሞክራቱ እጩ የአሜሪካን ግዙፍ ከተማ መምራት የቻሉ ሁለተኛው ጥቁር አሜሪካዊ ሆነዋል። አዳምስ ገና ታዳጊ ሳሉ በፖሊሶች አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።ታዲያ የፖሊስ አባል ከሆኑ በኃላ ለጥቁር የፖሊስ መኮንኖች መብት መከበርና ኢ ፍትሃዊነትን ሲታገሉ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በኒው ዮርክ የፖሊስ አያያዝና ወንጀል ዋንኛ ጉዳይ ሆኗል።
በስምኦን ደረጄ