
የሊቢያ አቃቤ ህግ የጋዳፊን ልጅ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሆኖ መቅረብ ተቃወመ
የሊቢያ ወታደራዊ አቃቤ ህግ መሀመድ ጋሮዳ የሀገሪቱ የቀድሞ ገዥ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሴይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ፕሬዚዳንታዊ እጩ ሆነዉ የሚያቀርቡበትን ሂደት እንዲያቆም የሊቢያ ብሄራዉ ምርጫ ኮሚሽንን ጠይቋል።አቃቤ ህጉ በተጨማሪም የጦር መሪ የሆኑት ካሊፋ ሃፍታር ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር እያደረጉ ያለዉን ጥረት እንዲታገድ ጠይቋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ እሁድ እለት እንዳስታወቀው የጋዳፊ ልጅ ለቀጣዩ ወር በሊቢያ በሚደረገዉ ምርጫ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሆነዉ ለመቅረብ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ማስገባታቸዉን ይፋ አድርጓል፡፡ነገር ግን ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ጋሮዳ ለምርጫ ኮሚሽኑ በጻፉት ደብዳቤ ሂደቱ ካልተገታ ኮሚሽኑ ለሚከትለው መዘዝ ተጠያቂ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ሰይፍ አል ኢስላም እና ካሊፋ ሃፍታር በወንጀል የተከሰሱ እንደመሆናቸዉ ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር የሚያደርጉት ጥረት መቆም አለበት ሲል የወታደራዊው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በደብዳቤዉ ገልጿል፡፡
የጋዳፊ ልጅ እጩ ሆነዉ መቅረብ የተጠበቀ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ በ2011 በፈጸሙት የጦር ወንጀሎች ክስ አሁንም በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ይፈለጋል።በሊቢያ የምስራቃዊ ሃይሎችን የሚመሩት ሃፍታር በጦርነቱ ወቅት ሊቢያውያንን በማሰቃየት ወንጀል በአሜሪካ ፍርድ ቤት ይፈለጋሉ።
በሚኪያስ ፀጋዬ