መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 7፣2014-በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ የወረዳ አስተዳደር ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል፡፡

በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ የነበረ የወረዳ አስተዳደር ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘሪሁን ተፈራ እንደገለፁት አንድ ግለሰብ ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ ሲንቀሳቀስ ህዝብ በሰጠው ጥቆማ በፖሊስ አባላት ተደርሶበት በተደረገ ምርመራ ሃሰተኛ መታወቂያውን ያዘጋጀውን ግለሰብ ማወቅና በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ ሃሰተኛ ሰነዶቹን የሚያዘጋጀው ተጠርጣሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ የስራ መደብ ላይ ይሰራ የነበረ እና በአሁኑ ወቅት በሌላ የስራ መደብ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሃሰተኛ ክብ ማህተም እና ቲተሮችን በማስቀረፅ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ህገ-ወጥ ሰነዶችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡

ዋና ኢንስፔክተር ዘሪሁን ተፈራ እንዳስረዱት የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ህዳር 04፣2014 ዓ/ም ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የረር በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ባደረገው ብርበራ የተለያዩ ንግድ ፈቃዶች፣ የትምህርት ማስረጃዎች ፣ መሸኛ ደብዳቤዎች፣ የጋብቻ ማስረጃዎች እና ሌሎች ልዩ ልዩ ሰነዶች ተገኝተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማህተሞች እና ቲተሮች፣ ፍላሾች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና ፎቶግራፍ የተለጠፈባቸውን ጨምሮ ለሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ መስሪያ የሚገለገልባቸው በርካታ ካርዶች እና ሃሰተኛ ሰነድ ሊዘጋጅባቸው የተሰጡ የበርካታ ግለሰቦች ፎቶ ግራፎች በብርበራ ተይዘዋል፡፡

ምንጭ፦ አዲስ አበባ ፖሊስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *