
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ወቅታዊ ሁኔታውን በመጠቀም የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ አካላትን እንደማይታገስ አስታወቀ
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ እንደ አመቺ አጋጣሚ በመጠቀም የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ አካላትን እንደማይታገስ የከተማ መስተዳድሩ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዮናስ ዘዉዴ ከብስራት ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊዉ ህብረተሰቡ ያለበትን የኢኮኖሚያዊ ጫና ግምት ዉስጥ ባለማስገባት አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች እና ትራንስፖርት ሰጪ አካላት ለግል ጥቅማቸዉ ሲባል አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን የሚያደርጉ እንዳሉ ተናግረዋል። ይህን መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ላይም በከተማዋ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ክትትል አድርጎ እርምጃ እንደሚወስድ አንስተዋል።
አቶ ዮናስ ጨምረዉም ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሀላፊዎች ወደ ግንባር እንዳቀኑት ሁሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማቸዉን በንቃት በመጠበቅ የአካባቢያቸውን ፀጥታ እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል።
እስካሁንም የከተማው ነዋሪ እያሳየ ያለዉ የነቃ ተሳትፎ በፖሊስ እየተያዙ የመጡ የጦር መሳሪያዎች እና ወንጀሎች እንዲጋለጡ እያደረጉ ያለ ሲሆን ህብረተሰቡ እያደረገ ያለዉን የነቃ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።
በበረከት ሞገስ