መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 16፤2014-በደብረብርሃን ከተማ የተላለፈው ክልከላ ተግባራዊ መደረግ ጀመረ

በደብረብርሃን ከተማ መታወቂያ ያልያዘ ሰዉ መንቀሳቀስ እንደማይችል በትናንትናው እለት የተላለፈዉ ክልከላ መተግበር መጀመሩን የከተማዋ ሰላም እና ደህንነት ጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል እሸቱ በተለይ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።

ሀላፊዉ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ተፈናቃይ እንዳለ አስታዉቀዉ በከተማዋ ተፈናቃይ በመምሰል የሚንቀሳቀሱ ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ዉሳኔዉ እንደተላለፈ ገልጸዋል ።አቶ ዳንኤል አያይዘዉም በተለያየ ጉዳይ በከተማዋ በስራ ላይ የሚገኙ ሌሎች ዜጎችን ክልከላዉ እንደማይመለከታቸው እና አስፈላጊዉን መረጃ ለፀጥታ አካላት በማሳየት በከተማዋ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተናግረዋል ።

በዛሬው እለት ተግባራዊ መደረግ በተጀመረው ክልከላም የከተማዋ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካሉ ጋር በመተባበር ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኝ እና ተፈናቃዮችም ወደተዘጋጀላቸው መጠለያ እየገቡ እንደሆነ ገልጸዋል። ክልከላዉ የተላለፈው ሌላዉን ማህበረሰብ ለማግለል ሳይሆን የከተማዋን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ነዉ ያሉት የከተማዋ ሰላም እና ደህንነት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ማህበረሰቡ መመሪያዉን በቀናነት በመተግበር ከተማዋን አጠናክሮ መጠበቅ እንዲቀጥል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *