በሰበታ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተከማቸ የጸጥታ አካላት አልባሳት በቁጥጥር ስር ዋለ
በሰበታ ከተማ መስተዳድር በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በርካታ የጦር መሳሪያዎች የጸጥታ አካላት አልባሳት ሀሰተኛ ማስረጃዎች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መያዛቸውን የሰበታ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል፡
የሰበታ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር አንተነህ ጌታነህ ለብስራት ሬድዮ እንደገለጹት ሰሞኑን በከተማው የጅማ በር እና የቡታጅራ መግቢያ በተደረገ ፍተሻ የብሬል እና የክላሽኮቭ ጥይቶች መያዛቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በከተማው ወረዳ 03 ውስጥ በአንድ ግለሰብ ቤት የተከማቸ የጸጥታ አካላት አልባሳት በብዛት የተገኘ ሲሆን የተለያዩ ማዕረጓች የታተሙባቸው፣የጸጥታ ሀይል ቀበቶዎች እና ዱላዎች መያዛቸው ተነግሯል።
እንዲሁም የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ፣ላፕቶፖች ፣የጦር ሜዳ መነጽሮችና ሀሰተኛ የማስረጃ ወረቀቶች ከነማህተዎቻቸው መያዛቸው ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል በከተማው በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ስምንት ሀሰተኛ መታወቂያ ወረቀቶች እና ከወሳኝ ኩነት ቢሮ የወጡ በማስመሰል የተዘጋጁ ሀሰተኛ የጋብቻ ፍቺ የምስክር ወረቀቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንስፔክተር አንተነህ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
በሳምራዊት ስዩም