
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት በአዲሱ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ኦሚክሮን የተነሳ በሀገራቸው ላይ የተጣለውን የጉዞ እገዳ አወገዙ
በደቡብ አፍሪካ እና በጎረቤቶቿ ላይ አዲሱን ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ኦሚክሮን ተከትሎ የተጣለውን የጉዞ እገዳ አውግዘዋል።ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በድርጊቱ በጣም አዝኛለሁ ፍትሃዊ አይደለም እገዳው በአስቸኳይ ሊነሳ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የጉዞ እገዳ ከጣሉት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮጳ ህብረት እና አሜሪካ ይገኙበታል።ኦሚክሮን የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን ቀደም ብለው የተሰሩ ምርምሮች እንዳመላከቱት በድጋሚ በቫይረሱ የመያዝ አደጋን እንደደቀነ ተነግሯል።
በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ አሰፋፈር ባለበት ጓውቴንግ ውስጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የቫይረሱ ተጠቂዎች ከተለዩ በኃላ አሁን ላይ በመላው የሀገሪቱ ግዛቶች እየተስፋፋ ይገኛል።የአለም የጤና ድርጅት በችኮላ የጉዞ ገደቦችን የሚጥሉ ሀገራትን በማስጠንቀቅ አደጋ ላይ የተመሰረት እና ሳይንሳዊ አካሄድን መመልከት አለባቸው ሲል አስታውቋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ለጉዞ እገዳው ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መሰረት እንደሌለና ደቡባ አፍሪካ የኢ-ፍትሃዊ አድሎ ሰለባ ሆናለች ሲሉ በትላንትናው እለት ተናግረዋል።እገዳ የጣሉ ሀገራት በኢኮኖሚያችን ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በስምኦን ደረጄ