
በኢትዮጵያ ከ15 ዓመት የእድሜ ክልል አንስቶ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመሩ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያል።ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ከ15 እስከ 64 የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች የትምባሆ ተጠቃሚ በመሆን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ሲል የኢትዮጵያ ምግብ መድሃኒት እና ጤና ክብካቤ እና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል ።
በባለስልጣኑ የትምባሆ ቁጥጥር ቡድን መሪው አቶ ባህሩ ዘውዴ እነዚህ አጫሾች ዛሬ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውን ለብስራት ሬድዮ የተናገሩ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የኢትዮጲያ ህዝብ 5 ከመቶው የሲጋራ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል ።
ከእነዚህ አጫሾች ውስጥ የአፋር ክልል 15 ከመቶውን በመውሰድ ቀዳሚ ሲሆን ጋምቤላ በ11.2 በመቶ ሁለተኛውን እንዲሁም ሀረር ደግሞ በ7.2 በመያዝ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚቀመጥ ሃላፊው አንስተዋል ።
ከአጠቃላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ 2.2 በመቶዎቹ ሲጋራ አጫሾች መሆናቸው በጥናቱ እንደተመላከተ አቶ ባህሩ ዘውዴ ተናግረዋል ።
በተጨማሪም ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተገናኘ 17 ሺህ ሞት በኢትዮጲያ በየዓመቱ እንደሚመዘገብ የተገለፀ ሲሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ 8 ሚሊዮን ገደማ ሞቶች ከሲጋራ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ መሆናቸው ተረጋግጧል ።
በዓለም ላይ በሲጋራ ማጨስ ምክንያት ከሚመዘገቡ ስምንት ሚሊዮን ሞት ውስጥ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት ባያጨሱም አጠገባቸው ባሉ አጫሾች ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉ ናቸው ሲሉ አቶ ባህሩ ዘውዴ ለጣቢያችን ተናግረዋል ።
በናትናኤል ሀብታሙ