መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 28፤2014-የኮሎምቢያ አማፂ ቡድን አዛዥ ኤል ፓይሳ በቬንዙዌላ ተገደለ

የኮሎምቢያ ፋርክ አማፂ ቡድን የቀድሞ መሪ በቬንዙዌላ በደረሰ ጥቃት መገደሉን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።በቬንዙዌላ አፑሬ ግዛት ውስጥ በቅፅል ስሙ ኤል ፓይሳ ተብሎ የሚጠራው ሄርናን ዳሪዮ ቬላስኬዝ በጥይት ተመቶ ተገድሏል።

በኤል ፓይስ የሞት ዜና ዙሪያ በይፋ ማረጋገጫ መስጠት ያልተቻለ ሲሆን የኮሎምቢያ ጦር ስለ ግድያው ምንም መረጃ እንደሌለው ተናግሯል።የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ግን ቅጥረኛ ነፍስ ገዳዮች ቬላስክዝን ገድለውት ሊሆን እንደሚችል እየዘገቡ ይገኛል፡፡

የኮሎምቢያ የመንግስት ባለስልጣናት ለኤል ቲምፖ ጋዜጣ እንደተናገሩት ከሆነ የኤል ፓይስን አስከሬን እስከምንመለከት ድረስ መሞቱን አናረጋግጥም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ኢቫን ዱኬ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የፕሬዝዳንቴ ፅህፈት ቤት በበኩሉ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እያፈላለገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፋርክ አማፅያን ከ50 ዓመታት በላይ በኮሎምቢያ መንግሥት ላይ መራራ ጦርነት ያካሄዱ የማርክሲስት ቡድን ነበሩ፣ በስተ መጨረሻም በ2016 የተኩስ አቁም በማድረግ ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ይታወሳል፡፡

በፋርክ ቡድን ዉስጥ በጣም ከሚፈሩ አዛዥ መካከል ቬላስክዝ አንዱ ሲጎን እ.ኤ.አ በ2003 በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ 36 ሰዎችን ለገደለው እና ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገዉ በመኪና ላይ የተጠመደ የቦምብ ጥቃት አቀነባባሪ ነበር፡፡

በሚኪያስ ጸጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *