መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 29፤2014-ባይደን ከፑቲን ጋር በነበራቸው የቀጥታ ውይይት የዩክሬን ውጥረት እንዳይባባስ አሳስበዋል❗️

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት የቀጥታ ውይይት ወታደራዊ ግጭት በዩክሬን ውጥረት እንዳይቀሰቀስ አሳስበዋል።ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ወታደራዊ አቅሟን ማጠናከሯ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ሁለቱ መሪዎች በቪዲዮ ያደረጉት ውይይት ሰላምታ ከመለዋወጥ መጀመራቸውን ከክሪምሊን ቤተ መንግስት ይፋ የተደረገው የቪዲዮ ማስረጃ ያሳያል።ባይደን በውይይቱ ላይ ፑቲንን በማየታቸው ደስ መሰኘታቸውን በመግለፅ በቀጣይ ውይይታችን በአካል እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

ከውይይታቸው በኃላ ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ ሩሲያ በዩክሬን ዙሪያ ወታደራዊ አቅሟን ማጠናከሯ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ አጋሮቿ ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው ባይደን ተናግረዋል።ለሩሲያ ድርጊት ጠንካራ የኢኮኖሚ እና ሌሎች እርምጃዎች ምላሽ እንደሚሰጡም አንስተዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ድጋፋቸውን ገልፀዋል።ዩክሬን በድንበሯ ላይ 94ሺ የሩሲያ ወታደሮች እንደሚገኙ አሳውቃለች።

ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው በሩሲያ ድንበሮች አቅራቢያ ያለውን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ኔቶ ወታደራዊ አቅም መጠናከርና የዩክሬን ግዛቶችን ለመቆጣጠር የሚደረገው አደገኛ ሙከራዎች እየተከላከሉ መሆኑ ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *