አሸባሪው ህውሃት በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ያደረሰውን ውድመት ለመጠገን በተለያዩ ሶስት አቅጣጫዎች ላይ የጥገና ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡የደረሱ ጉዳቶች ከፍተኛ የሆነ የመስመር መበጣጠሶች የመልዕክት ማስተላለፊያ መስመሮች ብልሽት እንዲሁም በከባድ መሳሪያ ተመተው የወደቁትን የኤሌክትሪክ ማማዎችን በአዲሰ የመቀየር እና የመትከል ስራዎች ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት የጥገና አገልግሎት መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በፍጥነት እየተሰራ ያለ ሲሆን በሸዋሮቢት መስመር አብዛኛዎቹ ከተሞች ከሚሴ ጨምሮ እሰከ ትላንት ከሰዓት ድረስ መስመሮቹን ማገናኘት መቻሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞገስ መኮነን ለብስራት ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለህበረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉት መስመሮች ጥገና በፍጥነት አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ያለ ሲሆን በዛሬው እለት እስከ ደሴ ድረስ ያለውን የኤሌክትሪክ መስመር ለማገናኘት እየተሰራ ይገኛል፡፡
አያይዘውም ሁለተኛው መስመር ከገረገራ እስከ ጋሸና ያለው ሲሆን የጥገና ስራ የተጀመረ ቢሆንም ይሄኛው የመስመር ክፍል ከፍተኛ የሚባል አደጋን ደርሶበታል፡፡በዚህም የተነሳ ለጥገና የተወሰኑ ቀናቶች እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡ ሶስተኛው ከሚሌ ወደ ባቲ ያለው መስመር ላይ ትልልቅ ሁለት የኤሌክትሪክ ማማዎች በከባድ መሳሪያ ተመተው የወደቁ ሲሆን እነሱንም በተመሳሳይ የመጠገን ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ እና ሁሉም መስመሮች በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስች፤ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሚኒኬሽን ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞገስ መኮነን ጨምረዉ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
በኤደን ሽመልስ