
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በኮቪድ 19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የታየባቸውን ቀላል የህመም ምልክቶች መነሻ በማድረግ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።ሙሉ ለሙሉ ክትባት የወሰዱት ራማፎሳ በትላንትናው እለት በኬፕ ታውን ለቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንይ ኤፍ ደብሊው ደ ክለርክ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ከታደሙ በኃላ የህመም ስሜት እንደተሰማቸው ተነግሯል።
የ69 ዓመቱ ሲሪል ራማፎሳ በኬፕታውን ራሳቸውን ለይተው የሚገኙ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ወታደራዊ ጤና ማዕከል ክትትል እያደረጉ ይገኛል።ለምክትላቸው ዴቪድ ማቡዛ ሁሉንም ኃላፊነታቸውን በውክልና ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በቫይረሱ መያዛቸው ይነገር እንጂ ልውጥ በሆነው አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ኦሚክሮን ስለመቃታቸው የተነገረ የለም።ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ወር በፊት በደቡብ አፍሪካ የተገኘው የቫይረሱ ዝርያ የበለጠ ተላላፊ መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት አሳድሯል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳና የስራ አጋሮቻቸው ባለፈው ሳምንት አራት የአፍሪካ ሀገራትን ከጎበኙ በኃላ ተደጋጋሚ ምርመራ ቢያደርጉም በወቅቱ ከቫይረሱ ነፃ ተብለው ነበር።ባለፉት 24 ሰዓት በደቡብ አፍሪካ ከ18ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል።
በስምኦን ደረጄ