
የሀዋሳ ከተማ መገለጫዎች ተደርገው ከሚወሰዱ መስህቦቿ አንዱ የሆነውን ፍቅር ሀይቅ ዙሪያ ለረጅም ዓመታት ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች ከሶስት ወራት በፊት ሱቆቻቸው ለመንገድ በሚል በድንገት በመፍረሱ ምክንያት ከሚሰሩበት ስፍራ መፈናቀላቸውን እና ያፈረሰው አካል እስካሁን ቦታውን ሳይሰራበት መቆየቱ ቅር እንዳሰኛቸው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ለመዝናናት በአካባቢው ይመጡ የነበሩ ወጣቶችም ቢሆኑ ቦታው የቀደመውን ገጽታ በማጣቱ የሱስ መናሃሪያ እየሆነ መምጣቱ አስከፍቶናል ይላሉ።
ቅሬታውን ተከትሎ ምላሻቸውን የሰጡት የከተማዋ ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ መመሪያ ሃላፊ አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ በአካባቢው የነበሩ ሱቆች ሊፈርሱ የቻሉት የሀይቅ ዳርቻ የማልማት ፕሮጀክት ውስጥ የፍቅር ሃይቅ በመካተቱ እና ከግለሰቦቹ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ መሆኑን በተለይ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
የተደራጁት ማህበራት ለአምስት አመት ብቻ በቦታው እንዲሰሩ ፍቃድ ያገኙ ሲሆን ግለሰቦቹ መውጣት ከነበረባቸው ጊዜ በላይ የቆዩ እና በቦታው ሲኖሩ ሃብት ያፈሩ ናቸው ብለዋል።የቆይታ ጊዜያቸውን ያልጨረሱ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ማህበራት ደግሞ ተለዋጭ ቦታዎች እንዲሰጣቸው መደረጉን ተናግረዋል።
በአካባቢው በጀልባ ስራ ላይ የተሰማሩ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ሃይቁ ላይ እንደሚሰሩ መግባባት ላይ መደረሱን በመግለፅ የሚቀርበው ቅሬታው ተገቢ አይደለም ብለዋል።የሀይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሚገነባው በከተማ እና በክልል መስተዳድር ሲሆን በታህሳስ አጋማሽ ወደ ስራ እንደሚገባና በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል ።
60 ዓመታትን ያስቆጠረችው ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከተሞች በዘመናዊ ማስተር ፕላን የተመሰረተች የመጀመሪያዋ ከተማ ነች፡፡
ቤተልሄም እሸቱ