
ሽብርተኛው የህውሃት ቡድን በወረራ ይዞ ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለባቸው የደቡብ ወሎ አከባዎች መካከል የንግድና የኢንዱስትሪ ኮሪደር የሆነችው ኮምቦልቻ ከተማ አንዷ ነች።የሽብር ቡድኑ በወረራ ከተማዋን ይዞ በቆየባቸው 36 ቀናት ውስጥ ያደረሳቸው ውደመቶች እና ኪሳራዎች ከፍተኛ እንደነበሩ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር አህመድ የሱፍ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ፡፡
የማህበረሰቡን ስነ ልቦና የሚጎዱ ተግባራትን ከመፈፀሙ ባለፈ ከፍተኛ ሊባሉ የሚችሉ ውድመቶችን ከጥቃቅን አንስቶ እስከ ከፍተኛ ፋብሪካዎች ላይ ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ከእዚህ ባለፈ ይህ የሽብር ቡድን ከከተማዋ ቢወጣም ዛሬም ድረስ በየገጠር መንደሩ እና በሌሎችም ስፍራዎች የሚገኙት አንዳንድ አባላቱ እየተለቀሙ ለህግ ተላልፈው እየተሰጡ እንደሚገኙ ኢንጅነር አህመድ የሱፍ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የሽብር ቡድን አባላት ነዋሪውን መስለው ለማምለጥ ከመሞከራቸው ባለፈ ከጫካ ፤ ከመቃብር ስፍራ እና ከውሃ መውረጃ ቱቦ ውስጥ ሳይቀር እየተያዙ ይገኛሉ ሲሉ ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡የሽብር ቡድኑ በከተማዋ ያደረሰውን ጉዳት ጠግኖ ኮምቦልቻ ወደምትታወቅበት የቀደመው የተነቃቃ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ማዕከልነቷ ለመመለስ እየተሰራ የሚገኘውን ስራ አቅሙ የሚችል ሁሉም ኢትዮጲያዊ ሊያግዝ ይገባል ሲሉ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኮምቦልቻ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተመራው የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት አማካይነት ከሽብርተኛው የህውሃት ቡድን እጅ ህዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ነፃ እንድትወጣ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ናትናኤል ሀብታሙ