
በሰሜናዊ የሄይቲ ከተማ ካፕ ሃይቲን ነዳጅ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አንድ የጭነት ተሽከርካሪ ፈንድቶ ቢያንስ 60 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ተሰምቷል።ከሟቾች በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ክፉኛ መጎዳታቸው የተነገረ ሲሆን የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት ተጎጂዎችን ለማከም የሚረዱ ተጨማሪ ባለሙያዎችና የህክምና ቁሳቁስ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
ፍንዳታው የተከሰተው ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ሲሆን በሄይቲ ሁለተኛ ግዙፉ ከተማ ካፕ ሃይቲን የደረሰ ነው።የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ፓትሪክ አልሞኖር በፍንዳታው በተከሰተው ፍርስራሽ ውስጥ አሁንም ተጎጂዎች ሊኖሩ ይችላል በሚል የነፍስ አድን ስራው መቀጠሉን ተናግረዋል።
አደጋው በሄይቲ መዲና ፖርት ኤ ፕሪንስ እና በሌሎች ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።የሄይቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆቭኔል ሞይስ በወርሃ ሀምሌ በውድቅት ሌሊት በተኙበት በ12 ጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ተከትሎ የወንጀለኛ ቡድኖች መበራከት እና አለመረጋጋቱ ጨምሯል።
በስምኦን ደረጄ