
በሰሜን ኢትዮጲያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የወደመውን የወረኢሉ ንግስት ዘውዲቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም በዛሬው እለት 6.8 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁሶች ወደ ስፍራዉ መላኩን የየካቲት 12 ሆስፒታል ሚዲካል ኮሌጅ አስታውቋል፡፡
ከሆስፒታሉ የተውጣጡ የህክምና ቡድን ከሳምንታት በፊት ውድመት የደረሰበትን የወረኢሉ ንግስት ዘውዲቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መጎብኘታቸውን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሚዲካል ኮሌጅ የህክምና አገልግሎት ጥራት ዳሬክተር ዶክተር በረከት ዘላለም ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መውደሙን ያረጋገጡ ሲሆን አስቸካይ የሚያስፈልገውን ግብዓት ልየታ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ለወደመው ለወረኢሉ ንግስት ዘውዲቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚውል ቁሳቁሶችን የየካቲት 12 ሆስፒታል ሰራተኞች በመተባበር አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸዉ 6.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ቦታ ድረስ ለማበርከትት ቡድኑ በዛሬዉ እለት ተንቀሳቅሷል፡፡
ከቁሳቁስ እርዳታው በተጨማሪ ሆስፒታሉ መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ የተለያዩ ሙያዊ እገዛዎችን ለማድረግ በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የሚመራና ከተለያዩ የህክምና ክፍሎች የተውጣጡ ሁለት የልዑካን ቡድን ተዋቅሮ በጦርነቱ የወደሙ ቦታዎች ድረስ ለመሄድ መዘጋጀታቸውንም ዶክተር በረከት ዘላለም ጨምረዉ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡
በትግስት ላቀዉ