መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 8፤2014-በሽብርተኛዉ ቡድን ህወኃት የተነሳ በአጣየ ከተማ የሚገኙ ባንኮች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ተነገረ

በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀዉ የህወኃት ቡድን በአጣየ ከተማ በቆየባቸዉ አስራ አምስት ቀናት ከፍተኛ ዉድመት ማድረሱ ተሰምቷል፡፡ከደረሱ የንብረት ዉድመቶች በተጨማሪ በወጋገን ባንክ በጥበቃ ስራ ላይ ያገለግል የነበረውን አረጋ ግዛው የተባለዉን ግለሰብ በመግደል አስክሬኑን ባንኩ ውሳጥ በመጣል ባንኩን ሙሉ ለሙሉ አዌድመዋል፡፡

ከቀናት በኃላ አስክሬኑን በማንሳት የሟች ቤተሰቦችን ማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ብስራት ሬድዮ ሰምቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቅርንጫፍ ባንኩን የማጽዳት ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ቡድኑ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የዝርፊያ እና ንብረት የማውደም ተግባር የተፈጸመ ሲሆን ባንኩን የህውሃት አባላቶች እንደ መጠለያ ይጠቀሙበት እንደነበረም ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጣየ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አድነው ከበደ እንደገለጹት ከሆነ ባንኩ ውስጥ የነበረው ገንዘብ ቀድሞ ለማውጣት የተቻለ ቢሆንም በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ቡድኑ ማድረሱን እንዲሁም የATM ማሽኖች ሙሉ ለሙሉ መዉደማቸዉን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ባንኩ አገልግሎት እንዲሰጥ የማጽዳት እና ሌሎች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።

አጣየ ከተማ በኦነግ ሸኔ ለተከታታይ ስድስት ጊዜያት ከደረሰባት ውድመት ሳታገግም የህወኃት ቡድን ለሰባተኛ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ወድማለች፡፡የአካባቢው ነዋሪዎችም ከተማዋ ላይ የስራ እንቅስቃስይ ያልተጀመረ በመሆኑ ንብረታቸውም በመውደሙ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ብስራት ሬድዮ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *