
በአዲስ አበባ የብዙሃን ትራንስፖርት ፣ የሚዲ ባስ (ሀይገርና ቅጥቅጥ) ፣ የከተማ ታክሲዎችን ጨምሮ 10,000 የሚሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ይገኛሉ። ይሁንና አሁንም ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር በቂ አለመሆኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ቅሬታ ነው።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ሰፊ ስራዎች እየከወነ ሲሆን ፤ ያለውን የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ዛሬ ይፋ በሆነው የታሪፍ ጭማሪም እነዚህ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጭማሪው ውስጥ እንዳይካተቱ አድርጓል።
በከተማዋ አሁን አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት በተለይም የከተማ ታክሲዎች አላግባብ የታሪፍ ጭማሪ ፣ ህገወጥ የመስመር ማቆራረጥ እና መስመርን አለመሸፈን እንደ መብት ማየት የተለመደ ነው።
መሰል ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ በቀጣይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ ለብስራት ተናግረዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት አገልግሎት ሰጪዎችን በሚመለከት ከ350በላይ የቁጥጥር ባለሙያዎች እንዳሉ በመጥቀስ ፤ ድንገተኛና መደበኛ ቁጥጥር ይደረጋል ከፍተኛ ቅጣትም ይኖረዋል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ ከ 300 በላይ ተሽከርካሪዎች የሚቀጡ ሲሆን ፤ በየቀኑ የሚቀጣው የተሽከርካሪ መጠን ቁጥር ቀደም ካሉት ጊዜያት ጨምሯል ነው ያሉት።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከትሎ ተግባራዊ የተደረጉ መመሪያዎችን የማያከብሩ የትራንስፖርት ዘርፉ አገልግሎት ሰጪዎች መኖራቸውንና ፣ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ቢሮው አሳስቧል።
በሚኪያስ ፀጋዬ