መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 12፤2014-አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የሀብት መጠኑ 2.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አስታወቀ!

ከአስራ አምስት አመታት በፊት ምስረታውን ያደረገው አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር በአሁን ሰዓት 62 ሺህ 522 አባላት በስሩ እንደሚገኙ የህብረት ስራ ማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ሸለመ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ።

ህብረት ስራ ማህበሩ ከምስረታው ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በተሰጠ 2.8 ቢሊዮን ብር ብድር አማካይነት የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ ሃላፊው ጨምረው አንስተዋል።

በዚህ ዓመት ህብረት ስራ ማህበሩ 103 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ሃላፊው የገለፁ ሲሆን በአጠቃላይ ከአባላቱ ብቻ ቁጠባን በመሰብሰብ የሃብት መጠኑን 2.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል።

አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር አስራ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዘንድሮ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል።

ከተገኘው 103 ሚሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ 30 በመቶ የመጠባበቂያ እንዲሁም 5 በመቶ ለማህበራዊ አገልግሎት ተቀንሶ ለአባላቱ በአንድ ሼር 30 በመቶ የትርፍ ክፍፍል ተሰጥቷል።

ያም ቢሆን ግን ህብረት ስራ ማህበሩ የመሬት ጥያቄን በተደጋጋሚ ለመንግስት ቢያቀርብም ምላሽ ባለማግኘቱ ዛሬም ድረስ በግለሰብ ቢሮ ውስጥ ተከራይተን ለመስራት ተገደናል ሲሉ አቶ ዘሪሁን ሸለመ ተናግረዋል ።

በናትናኤል ሀብታሙ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *