
በደቡባዊ ባንግላዲሽ በአንዲት መርከብ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 37 ሰዎች ሲሞቱ 100 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸዉን የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት አስታዉቀዋል፡፡አደጋዉ የደረሰበት ባለ ሶስት ፎቅ መርከብ ላይ ሲሆን ቃጠሎው የጀመረው ከዋና ከተማው ዳካ ወደ ባርጉና ከተማ ሲጓዝ በጃላካቲ በተባለች ከተማ አቅራቢያ ነዉ ፡፡
አንዳንድ የመርከቧ ተሰፋሪዎች አደጋዉን ለማምለጥ ዘለዉ ወደ ውሃ ውስጥ ሲገቡ ሰጥመዉ ህይወታቸዉ ሳያልፍ እንዳልቀረም ተዘግቧል፡፡፡በዛሬዉ እለት በደረሰው አደጋ የተጎጂዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በመርከቧ ውስጥ 500 የሚደርሱ ሰዎች ተሳፍረዉ ነበር የተባለ ሲሆን የባንግላዴሽ የእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት ባለስልጣን ካማል ሆሳይን ቡዪያን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት እሳቱ በመርከቡ የሞተር ክፍል ውስጥ ተነስቶ በፍጥነት መዛመቱን ገልጸዋል፡፡
እሳቱ ከተነሳ በኃላ ለሰዓታት መቀጠሉ እማኞች ተናግረዋል፡፡ በህይወት የተረፉ አንድ ተሳፋሪ፣ አዛዉንት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት እሳቱ በተነሳበት ወቅት አብዛኛው ሰው ተኝቶ ነበር።በመርከቡ ወለል ላይ ባለው ምንጣፍ ላይ ተኝተን ነበር የ9 ዓመቱ የልጅ ልጄ ናኢም ከእኔ ጋር ነበር፣እሳቱን እንደተነሳ ወደ ወንዙ ዘሎ ገባ። ምን እንደደረሰበት አላውቅም ሲሉ እኚሁ አዛዉንት ተናግረዋል።
አደጋዉን የሚያጣራ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ባርጉና ከባንግላዴሽ መዲና ዳካ በስተደቡብ በ250 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡በ2020 በዳካ ከተማ አቅራቢያ ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ ሰጥማ በርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
በስምኦን ደረጄ